የዩኒቨርሲቲው የምርምር ጣቢያ ከተሻሻሉ የእንስሳት መኖና የግብርና አሰራሮች ጋር አስተዋውቆናል---- ከፊል አርብቶ አደሮች

90

ጎባ  የካቲት 27/2011 በመዳ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ የተከፈተው የምርምር ጣቢያ ከተሻሻሉ የእንስሳት መኖና የግብርና አሰራሮች ጋር እንዳስተዋወቃቸው የመዳ ወላቡ ወረዳ ከፊል አርብቶ አደሮች።

ዩኒቨርሲቲው በበኩሉ በተቋሙ የተከፈቱ ሦስት የምርምር ጣቢያዎች የእውቀት ሽግግር በማድረግ ላይ መሆናቸውን አስታውቋል።

የመዳ ወላቡ ወረዳ ከፊል አርብቶ አደሮች ለኢዜአ እንደገለጹት በዩኒቨርሲቲው የተከፈተው የምርምር ጣቢያ ከተሻሻሉ የእንስሳት መኖ ዝርያዎች፣ ከዘመናዊ የእንስሳት አረባብ ዘዴና የግብርና አሰራሮች ጋር አስተዋውቋቸዋል።

ከወረዳው ነዋሪዎች መካከል ከፊል አርብቶ አደር አህመድ አልይ እንደተናገሩት ካለፉት አምስት ዓመታት በፊት በበባህላዊ  መንገድ ካረቧቸው የቀንድ ከብቶች የልፋታቸውን ያህል ተጠቃሚ አልነበሩም።

ከምርምር ጣቢያው ያገኙትን እውቀት ተግባራዊ በማድረግ በዚህ ዓመት ብቻ በዘመናዊ መልኩ በአካባቢያቸው የደለቡ ሰንጋዎችን ለገበያ በማቅረብ 50 ሺህ ብር ገቢ ማግኘታቸውን አስረድተዋል።

የወረዳው ነዋሪ ከፊል አርብቶ አደር ሱሌይማን ሀሰን የምርምር ጣቢያ ከባህላዊ የግብርና አሰራር በመላቀቅ የተሻሻሉ የግብርና አሰራሮችን ተግባራዊ እንዲያደርጉ ያገዛቸው መሆኑ ገልጸዋል።

በእዚህም ከአንድ ሄክታር ያገኙት የነበረውን 25 ኩንታል የስንዴ ምርት በእጥፍ ለማሳደግ መቻላቸውን ተናግረዋል።

ሌላው የወረዳው ነዋሪ ከፊል አርብቶ አደር በድሪ ጀማል በበኩላቸው የምርምር ጣቢያው በመስመር የመዝራት ቴክኖሎጂን ጨምሮ ከሌሎች የተሻሻሉ የግብርና አሰራሮች ጋር ያስተዋወቃቸው መሆኑን ጠቁመዋል።

የተሻሻሉ የግብርና አሰራሮችን በመጠቀም በመኽሩ ወቅት በአንድ ተኩል ሄክታር ማሳቸው ላይ ካመረቷቸው የማሾና ሰሊጥ ሰብሎች ላይ የተሻለ ምርት በመሰብሰብ ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የመዳ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ የምርምር፣ ማህበረሰብ አቀፍና የቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ስሜነህ ቤሴ ዩኒቨርሲቲው የአርሶና አርብቶ አደሩን ማህበረሰብ ፍላጎት መሰረት ያደረጉ ምርምሮችን በቅርበት ለማካሄድ የሚያስችሉ ሦስት የምርምር ጣቢያዎችን ከፍቶ በመስራት ላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የምርምር ጣቢያዎቹ በቅርበት አገልግሎት እየሰጡ ያሉት በሮቤ፣ መዳ ወላቡና ጊኒር ወረዳዎች ውስጥ ለሚገኙ አርሶና አርብቶ አደሮች መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው በከፈታቸው የምርምር ጣቢያዎች ከተለያዩ የግብርና ምርምር ተቋማት የተለቀቁ አዳዲስ ዝርያዎችን ከአካባቢው ስነ ምህዳር ጋር በማላመድ የአርሶና አርብቶ አደሩን ማህበረሰብ ችግር ለመቅረፍ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

ዩኒቨርሲቲው በአሁኑ ወቅት የአካባቢውን ማህበረሰብ ፍላጎት መሰረት ያደረጉ ከ58 የሚበልጡ ምርምሮችን በማካሄድ ላይ መሆኑንም አስታውቀዋል።

የመዳ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ከ1999 ዓ.ም ወዲህ በተለያዩ መስኮች ላይ ያተኮሩ ከ200 የሚበልጡ የምርምር ስራዎችን ማከናወኑን ከዩኒቨርሲቲው የተገኛ መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም