በመስኖ ልማት በመሰማራት ከዝናብ ጥገኝነት ተላቀው ኑሯቸው መሻሻሉን የማዕከላዊ ጎንደር አርሶአደሮች ገለጹ

43
ጎንደር ግንቦት 22/2010 በመስኖ ልማት መሰማራታቸው የዝናብ ጥገኛ በመሆን ከእጅ ወደ አፍ የነበረው ኑሯቸው እንዲለወጥ ማድረጉን በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የሚገኙ መስኖ አልሚ አርሶአደሮች ተናገሩ፡፡ የዞኑ ግብርና መምሪያ በበኩሉ በዞኑ በዘንድሮ የበጋ ወራት በመስኖ ከለማው መሬት ከ7 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰቡን አስታውቋል፡፡ በጎንደር ዙሪያ ወረዳ የጽዮን ቀበሌ ነዋሪ አርሶአደር ወርቁ ግርማ እንዳሉት ወደ መስኖ ሥራ ከመግባታቸው በፊት ከመኸር እርሻ ብቻ በሚያገኙት ምርት የቤተሰባቸውን የዓመት ቀለብ ለመሸፈን ተቸግረው ነበር፡፡ "ከአራት ዓመት በፊት አንድ የውሃ መሳቢያ ሞተር በብድር ገዝቼ የጀመርኩት የመስኖ ልማት ሥራ በአሁኑ ወቅት 11 የውሃ መሳቢያ ሞተሮችን በመግዛት አራት ሄክታር መሬት በማልማት ኑሮዬን መቀየር ችያለሁ" ብለዋል፡፡ የሳር ክዳን ጎጇቸውን ወደ ቆርቆሮ ክዳን ቤት ከመቀየር ባለፈ 120ሺህ ብር በጥሬ ገንዘብ በቁጠባ ለማስቀመጥ መብቃታቸውንም ተናግረዋል፡፡ በዘንድሮ የበጋ ወራትም በመስኖ ያለሙትን ከ40 ኩንታል በላይ ነጭ ሽንኩርት ለገበያ በማቅረብ ከ50 ሺህ ብር በላይ ገቢ በማግኘት ተጠቃሚ መሆናቸውን ነው አርሶአደር ወርቁ የገለጹት፡፡ "በመስኖ ሥራ ሕይወቴ እየተቀየረ ነው፤ የሁለት የእርሻ በሬ ባለቤት ከመሆን ባለፈ የቆርቆሮ ክዳን መኖሪያ ቤት ሰርቺያለሁ" በማለት የተናገሩት ደግሞ የጎንደር ዙሪያ ወረዳ ነዋሪ አርሶአደር ሲሳይ ተሻገር ናቸው፡፡ ዘንድሮ በግማሽ ሄክታር መሬት ያለሙትን 35 ኩንታል ቀይ ሽንኩርት በገበያ ሽጠው 28 ሺህ ብር ገቢ ማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡ በታች አርማጭሆ ወረዳ የአንገረብ ወንዝን በመጠቀም ከሁለት ዓመት በፊት ወደ መስኖ ሥራ የገባው ወጣት መንግስቱ ጣሰው በበኩሉ ዘንድሮ በመስኖ ካለማው ቲማቲም ከ50 ሺህ ብር በላይ ገቢ ማግኘቱን ተናግሯል፡፡ ተጨማሪ የውሃ መሳቢያ ሞተሮችን በመግዛት የመስኖ ስራውን የማስፋት ዕቅድ እንዳለው የተናገረው ወጣቱ ወደ መስኖ ሥራ ከመግባቱ በፊት ለሦስት ዓመታት የቤተሰብ ጥገኛ ሆኖ ማሳለፉን ተናግሯል፡፡ በዘንድሮ የበጋ ወራት በወረዳው በመስኖ ከለማው 14 ሺህ ሄክታር መሬት ከ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መገኘቱን የገለጹት ደግሞ የጎንደር ዙሪያ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ አራጋው ተፈራ ናቸው፡፡ የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ግዛቸው ጀመረ በበኩላቸው በዘንድሮ የበጋ ወራት ከ200 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች በመስኖ ልማት ሥራው ማሳተፋቸውን ተናግረዋል፡፡ በዞኑ የተለያዩ ወረዳዎች በመስኖ ከለማው 62 ሺህ ሄክታር መሬት 7 ነጥብ 7 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማምረት ታቅዶ 7 ነጥብ 1 ሚሊዮን ኩንታል ምርት መመረቱን ተናግረዋል፡፡ "አርሶ አደሩ በገበያ ተፈላጊ የሆኑትን የጓሮ አትክልቶች ጨምሮ የቢራ ገብስ፣ ስንዴ፣ በቆሎና ሽንብራ በማምረት ለራሱ ፍጆታም ሆነ ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆን ችሏል" ብለዋል፡፡ ለመስኖ ሥራው ከ13 ሺህ ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ጥቅም ላይ መዋሉን የጠቆሙት ኃላፊው፣ በመስኖ ልማት በመስመር የመዝራት ቴክኖሎጂን አርሶአደሩ እንዲጠቀም መደረጉን ገልጸዋል፡፡ ልማዳዊና ውሃባካኝ የመስኖ ውሃ አጠጣጥን የሚቀይር ዘመናዊ የውሃ ማጠጫ ቴክኖሎጂን ለአርሶአደሩ በማስተዋወቅ በውሃ እጦት በመስኖ ሰብሎች ላይ የሚደርስውን የምርት መቀነስ ለማስቀረት ጥረት መደረጉንም ተናግረዋል። አርሶአደሩ በገበያ አዋጭና እንደ አካባቢው ስነ ምህዳር ተስማሚ የሆኑ ምርቶችን ለይቶ በማምረት የገበያ ዋጋ መውደቅን ለመከላከል የሚያስችል ሥራ መሰራቱንም አቶ ግዛቸው አስታውቋል፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም