የአድዋ ጦር መንገዶች

140

አዲስ አበባ የካቲት 26/2011 ከአድዋ ዘመቻ ታሪካዊ ስፍራዎች ጉብኝት ጎብኝዎች ምን ታዘቡ?

የኢትዮጵዊያን ብሎም የመላው ጥቁር ህዝቦች ድል የሆነው የአድዋ ድል በዓል ባለፈው ሳምንት ማብቂያ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በተለያዩ ዝግጅቶች ተዘክሯል።

ድሉ ከተዘከረባቸው መንገዶች መካከል በባህልና ቱሪዝም ሚኒቴር አዘጋጅነት ከአድዋ ጦርነት ጋር የተያያዙ ስፍራዎችን 'ከሸዋ አስከ አድዋ' በሚል መሪ ሃሳብ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ያካተተ ግብኝት ይገኝበታል። 

ጎብኚ ቡድኑ ለ5 ቀናት ጉብኝቱን አድርጎ በመጨረሻም በዓሉን አድዋ ላይ በማክበር ተመልሷል።

በዚህም ዳግማዊ አጼ ምኒልክና ፊታውራሪ ገበየሁ የትውልድ ስፍራ፣ የፊታውራሪ ገበየሁ አጽም የሚገኝበትን አንጎለላ ኪዳነ ምህረትና በስፍራው የሚገኘውን የየንጉስ ሣህለ ሥላሴ ፍርስራሽ ቤተ መንግስትና የአንኮበር ታሪካዊ ስፍራን ተመልክቷል።

ዳግማዊ አጼ ምኒልክ የክተት አዋጅ የጠሩበትን በደቡብ ወሎ ዞን የሚገኘውን የወረኢሉ ታሪካዊ ስፍራና የዳግማዊ አጼ ምኒልክ ቤተ መንግስት፣ የውጫሌ ውል የተፈረመበትን የይስማ ንጉስ ታሪካዊ ስፍራም የጉብኝቱ አካል ነበሩ።

ከአድዋ ጦር ጋር ታሪካዊ ትስስር ያላቸው የማይጨው ደብረ ጽጌ አቡነ ተክለሃይማኖት ገዳም፣ በመቀሌው ጦርነት ወቅት የስትራቴጂ ቦታ የነበረችዋን 'የማይ አንሽታይ' ምንጭና በቆላ ተንቤን የሚገኙ ታሪካዊ ስፍራዎችም በቡድኑ ተጎብኝተዋል።

የጉብኝቱ ተሳታፊዎች መካካል ለኢዜአ አስተያይታቸውን የሰጡ ታሪካዊ ስፍራዎቹና ታሪካዊ ሁነቶች በአግባቡ መተዋወቅ፣ መዘከርና ለቱሪስት መዳረሻነት መልማት ሲገባቸው የተሰራው ግን ከዚህ ግባ የሚባል አለመሆኑን ነው ያነሱት። 

ከጋምቤላ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ባለሙያ የሆኑት አቶ ቻም ኩሬን ከዚህ በፊት በሚዲያ ከተመለከቱት ይልቅ ታሪካዊ ስፍራዎችን በቦታው ተገኝተው በመመልከታቸው መደሰታቸውን ገልጸው፤ "ጀግኖች አባቶቻችን አጥንታቸውን ከስክሰው፤ ደማችውን አፍስሰው ያገኙት ድል ለመላው ጥቁሮች አኩሪ ድል ነው" ብለዋል።

ታሪካዊ ስፍራዎቹ የኢትዮጵያዊያን አንድነት ማሳያ እንደሆኑ ገልጸው፤ ወጣቱ ትውልድ ከጀግኖች አባቶች ትምህርት መውሰድ እንዳለበት ያስረዳሉ።

የኢትዮጵያ ደራሲያን ማኅበርን ወክላ የተጓዘችው ደራሲ የሽወርቅ ወልዴ የጥቁር ህዝብ ታላቅነት ያስመሰከረው አድዋ፣ ሕብረ ማንነት ያላቸው፣ በሚገባ የማይተዋወቁ ኢትዮጰያዊያን በእግር ተጉዘው በመስዋትነት አገርን ያስከበሩበት ድል መሆኑን ትገልጻለች።

የፊልምና ተያትር ባለሙያው አርቲስት ቢኒያም ወርቁ ታሪካዊ ስፍራዎችን በዘመቻ ስራ ሳይሆን ማልማትና ያለማቋረጥ ማስተዋወቅ እንደሚገባ ገልጾ፣ ዶክመተሪዎች፣ፊልሞችና ተአትሮች ሊሰራባቸው እንዳሰበ ይናገራል።

የደቡብ ወሎ ዞን አባት አርበኞች ማህበር ዋና ጸሃፊ አቶ አየለ ወልደጊዮርጊስ ዓለምን ያስደነቀው የአድዋ ድል ዳግማዊ አጼ ምኒልክ ከአራቱም ማዕዘን ዘር፣ ጎሳ፣ ሃይማኖት ሳይለዩ በክተት አዋጅ ብቻ ሎጀስቲክስ በሌለበት ወደ አድዋ ያዘመቱበት ታሪካዊ ሁነት ነው ይላሉ።

በደቡብ ወሎ ከሚገኙ ታሪካዊ ስፍራዎች መካከል ለጦርነቱ መንስኤ የሆነው የውጫሌ ውል የተፈረመበት የይስማ ንጉስና ዳግማዊ አጼ ምኒልክን ሰራዊታቸው እንዲሰባሰብ ክተት አዋጅ የጠሩበት ወረኢሉ ስፍራ እንደሆነ ያስረዳሉ።

የፋሽስት ጦርን ማሸነፍ የተቻለው በአንድነትና በወኔ እንጂ በዘመናዊ መሳሪያ ትጥቅ እንዳልሆነ የሚገልጹት አባት አርበኛው፣ ወጣቱ አገራዊ አንድነት እንዲኖረው የአባቶችን ታሪክና ታሪካዊ ስፍራዎችን በማወቅ አገሩን በቅንነት ማገልገል እንዳለበት ነው የሚመክሩት። 

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ጉዞው ታሪኩን ለመዘከር ብቻ ሳይሆን ታሪካዊ ስፍራዎችን ለቱሪስት መዳረሻነት ለማልማት የዕቅድ መነሻ የመያዝ ዓላማ ያለው መሆኑን ገልጸዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ዋናው ጦርነት የተካሄደበትን የአድዋ የጦር አውድማዎችን ጨምሮ የይስማ ንጉስ፣ አንጎለላና ሌሎች ታሪካዊ ስፍራዎች የቱሪስት መዳረሻ እንዲሆኑ የማድረግ ጅምር ስራ እንዳለ በጉብኝቱ መታዘብ ተችሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም