የህጻናትን መብትና ደህንነት የሚያስጠብቁ ተግባራት ውጤታማነት በባለቤትነት ስሜት እንዲሰራ ተጠየቀ

77

አዳማ የካቲት 26/2011 የህጻናትን መብትና ደህንነት ለሚያስጠብቁ ተግባራት ውጤታማነት ኅብረተሰቡና ባለድርሻ አካላት በባለቤትነት ስሜት እንዲንቀሳቀሱ የሴቶች ፣ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስትሯ ጠየቁ።

የህጻናት ጉዳይን ተቋማዊ ለማድረግና የህጻናት ፓርላማዎችን በሚጠናከሩበት ሁኔታ ላይ የሚመክር አገር አቀፍ መድረክ ዛሬ በአዳማ ከተማ ተጀምሯል።

ሚኒስትሯ ወይዘሮ ያለም ፀጋይ በመድረኩ ላይ እንዳስገነዘቡት ሕዝቡ ባለድርሻ አካላት በባለቤትነት ስሜት ህጻናት ከአገሪቱ ዘላቂ ልማትና እድገት ዋነኛ ተጠቃሚ እንዲሆኑ መሥራት ይገባል።

መንግሥት የህጻናትን መብት ለማስጠበቅ ፖሊሲና የአፈፃፀም መመሪያዎችን ከተዘጋጁ ረጅም ጊዜ ማስቆጠሩን ያወሱት ሚኒስትሯ፣ሆኖም ህፃናት የሥነ ልቡናና የማህበራዊ አገልግሎት እንዲያገኙ በማድረግ መብቶቻቸውን ማስከበር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

የሕጻናትን መብቶች በተሻለ እንዲጠበቁ የተከናወነው ሥራ አጥጋቢ እንዳልሆነና ክፍተቶቹን በማየት ህፃናት የተሻለ እድገት እንዲኖራቸውና ከችግር ማውጣት በሚቻልባቸው መንገዶች ለመነገጋር መድረኩ መዘጋጀቱን ሚኒስትሯ ጠቁመዋል።

በተለይ በድህነትና በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ያሉ ህጻናትን  ኑሮ ለማሻሻል ኅብረተሰቡ የጉዳዩ ዋነኛ ባለቤት እንዲሆንም  ጠይቀዋል።

ባለድርሻ አካላትም በባለቤትነት ስሜት ህጻናት ከአገሪቱ ዘላቂ ልማትና እድገት ዋነኛ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ሊሰሩ ይገባል ያሉት ሚኒስትሯ በተለይ የህጻናትን ተሳትፎ ለማጎልበት እንዲረባረቡ አሳስበዋል።

በየክልሉ የማገገሚያ ማዕከላትን በመገንባት በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ የሚገኙ ህፃናትን በመደገፍና በመንከባከብ እንዲሁም ከጥቃትና ብዝበዛ በመጠበቅ መሥራት ይጠበቅባችኋል ብለዋል።

የድግግሞሽ ስራን በማስቀረት አንድም ህጻን ወደ ጎዳና ላይ እንዳይወጣ ትኩረት ሰጥተው በቅንጅት እንዲሰሩ አሳስበዋል።

በሚኒስቴሩ የህጻናት መብት ዳይሬክተር አቶ ክብሪ ኃይሉ በመድረኩ ላይ ባቀረቡት ብሄራዊ የህጻናት ፖሊሲ መሰረት ከሕፃናት የሲቪል ነፃነትና ጥበቃ መብቶችመካከል ከጥቃት፣ብዝበዛና አካላዊ ቅጣት የመጠበቅ ይገኙበታል።

እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃበህፃናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችና የሚፈጸሙ ጥፋቶች እንዲወገዱ አስፈፃሚው አካልና ኅብረተሰቡ ለደህንነታቸው መጠበቅና ለመብቶቻቸው መከበር ቅድሚያ ትኩረት ሰጥቶ  መስራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ 

ፖሊሲው ተፈጻሚ እንዲሆንም በህፃናት ፓርላማዎች ትየህፃናትን ተሳትፎ ማሳደግ ወሳኝ መሆኑን አስታውቀዋል።

ህፃናት በቀላሉ ለጉዳት የተጋለጡ ናቸው ያሉት ዳይሬክተሩ ከዚህ ችግር ለማላቀቅ ማህበረሰብ አቀፍ ድጋፍና ክትትል አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ለሁለት ቀናት በሚቆየው መድረክ ላይ ከፌዴራል መንግሥትና ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም