የብአዴን ድርጅታዊ ኮንፍረንስ በባህር ዳር ከተማ በመካሄድ ላይ ነው

125
ባህር ዳር ሚያዝያ 28/2010 በክልልና በአገር ደረጃ የተጀመሩ የልማት ስራዎች ቀጣይነት እንዲኖራቸው በአመራሩ መካከል ጠንካራ የአስተሳሰብ አንድነት ሊኖር እንደሚገባ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የብአዴን ሊቀመንበር አቶ ደመቀ መኮንን ገለጸ። “የተሃድሶ ንቅናቄያችንን የበለጠ በማጥለቅ፣ በማስፋትና  ቀጣይነተቱን በማረጋገጥ  የህዝባችንን  የለውጥ ተስፋ እናስቀጥል!!” በሚል መሪ ሃሳብ የብሄረ  አማራ  ዴሞክራሲ ንቅናቄ /ብአዴን/ ድርጅታዊ ኮንፈረንስ ትናንት በባህር ዳር ተጀምሯል። ሊቀመንበሩ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት በኢህአዴግ  ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የተካሄደውን ግምገማ መሰረት በማድረግ የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴም የራሱን ጥልቅ ውይይት አድርጎ ክፍተቶችን ለይቷል። የኮንፈረንሱ አላማም በተለዩትና በታመነባቸው ጉዳዮች ዙሪያ በየደረጃው ካለው የድርጅቱ አመራር ጋር የበለጠ መግባባት ለመፍጠር ታስቦ መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡ በአመራር ደረጃ የሚስተዋለውን ለልማት ጸር የሆነውን የአስተሳሰብ ልዩነት ለማጥበብና  የአመራሩን የአስተሳሰብ  አንድነት ለማጠናከር የሚያስችል ውይይት እንደሚካሄድም ገልፀዋል፡፡ እንዲሁም በክልልም ሆነ በአገር ደረጃ  የሚታየውን ለውጥ ለማስቀጠል እንቅፋት በሆኑ ችግሮች ላይ ውይይት በማካሄድ የመፍትሄ አቅጣጫዎች  ይቀመጣሉ። ችግሮችን በጠንካራ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ለመፍታትና ተደማሪ ውጤት ለማስመዝገብ የድርጅቱ አመራሮችና አበላት በግንባር ቀደምትነት ሊንቀሳቀሱ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡ ለሦስት ቀናት በሚቆየው የብአዴን ድርጅታዊ ኮንፈረንስ በተለዩ ችግሮች ዙሪያ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ ለውጤታማነቱ አባላት ተልዕኳቸውን እንዲወጡ የሚያደርግ አቅጣጫ ያስቀምጣል ተብሎ ይጠበቃል። በውይይት መድረኩ ላይ  ከፍተኛና መካከለኛ አመራሩን ጨምሮ ሌሎች የድርጅቱ አባላት ተሳታፊ ሆነዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም