ፍርድ ቤቱ በእነ ሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው ላይ በሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ የተመሰረተው ክስ እንዲሻሻል ትዕዛዝ ሰጠ

67

አዲስ አበባ የካቲት 26/2011 ዐቃቤ ሕግ በእነ ሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው በ'ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ በመስጠት' ላይ የተመሰረተውን ክስ እንዲያሻሽል የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 15ኛ ወንጀል ችሎት ዛሬ ትዕዛዝ ሰጠ።

''የመከላከያ ኢንጂነሪንግ ኮሌጅ ባላስተማራቸውና ባልተቀረጸ ሥርዓተ ትምህርት ሐሰተኛ የሁለተኛና የሦስተኛ ዲግሪ እንዲሰጥ አድርገዋል'' በተባሉ ስምንት ተጠርጣሪ የቀድሞ የብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ (ሜቴክ) የስራ ሃላፊዎች ላይ ዐቃቤ ሕግ ክስ መመስረቱ ይታወቃል።

በአሜሪካ አገር ከሚታወቀውና በዓለም ላይ አሉ ከሚባሉ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ አንዱ ከሆነው 'ካሊፎርኒያ ኢንስቲትዩት ኦፍ ቴክኖሎጂ' ጋር ተቀራራቢ ስም ያለው ተቋም፤ ሆኖም ግን በማንም ዘንድ የማይታወቅ በሁለተኛና በሦስተኛ ዲግሪ ለማስተማር ዶክተር መኮንን ገብረሚካኤል ለተባለ ተጠርጣሪና በቁጥጥር ስር ካልዋለ አንድ ግለሰብ ጋር ሐሰተኛ የትምህርት ተቋሙ እንደተከፈተ የዐቃቤ ህግ ክስ ያስረዳል።

ተጠርጣሪ ዶክተር መኮንን ገብረሚካኤል ራሳቸውን የትምህርት ተቋሙ ሥራ አስኪያጅ አድርገው በማቅረብ፣  ከቀድሞ የሜቴክ የሥራ ኃላፊዎች ጋር በጥቅም በመመሳጠር በሐሰተኛ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ስም ከሜቴክ ጋር ለማስተማር የውል ስምምነት መፈራረሙንና የቀድሞ ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው ማጽደቃቸውን የዐቃቤ ሕግ ክስ አመልክቷል። 

ከሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው በተጨማሪ ብርጋዴር ጄኔራል ጥጋቡ ፈትለ፣ ሻለቃ ገብረሥላሴ ገብረጊዮርጊስ፣ ሻለቃ ፋሲል አበራ፣ መቶ አለቃ ቶማስ ደረሰ፣ ወሰንየለህ ኃይለሚካኤል እና ሀድአት ወልደትንሳይ ከሐሰተኛ ትምህርት ተቋሙ ጋር በተያያዘ የውል ስምምነት በመፈራረም ተጠርጥረዋል።

በመሆኑም ዐቃቤ ሕግ ባቀረበው የክስ ማመልከቻ ላይ ሐሰተኛ ተቋም ተብሎ የቀረበውና ከሜቴክ ጋር የተደረገው የግዢ ውል ስምምነት ጥሰትን በተመለከተ ክሱ ተሻሽሎ ለመጋቢት 4 ቀን 2011 ዓ. ም እንዲቀርብ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም