በኢትዮጵያ የቆላ ስንዴን በመስኖ የማልማት ሥራ እየተስፋፋ ነው

112

አዳማ የካቲት 26/2011 በኢትዮጵያ በአነስተኛ ማሳ ላይ የተጀመረውን የቆላ ስንዴ በመስኖ የማልማት ሥራ በቀጣዩ ዓመት ወደ100 ሺህ ሄክታር መሬት ለማስፋት መታቀዱን የወረር ግብርና ምርምር ማዕከል አስታወቀ።

በማዕከሉ የግብርና ኤክስቴንሽንና ኮሚዩኒኬሽን ተመራማሪና የሥራ ሂደቱ ባለቤት አቶ አደም ከድርለኢዜአ እንደገለፁት የቆላ ስንዴን በመስኖ የማልማት ሥራ በአንዲት ሴት አርብቶ አደር ሦስት ሄክታር ማሳ ላይ በሙከራ ደረጃ ማምረት የተጀመረው በ2006 ዓ.ም ነው።

ሀገር አቀፍ የቆላ ስንዴ ምርምር ማስተባበሪያ ሆኖ እየሰራ ያለው ማዕከሉ እስካሁን ድረስ ስምንት የቆላ ስንዴ ዝርያዎችን በምርምር ማውጣቱን ተናግረዋል።

ማዕክሉ ወደ ሰርቶ ማሳያ ሥራ ሊሸጋገር "አይቻልም" የሚል ሀሳብ ተነስቶበት እንደነበር ያስታወሱት አቶ አደም በአርብቶ አደሯ ማሳ ላይ በተደረገው ሙከራ በሄክታር በአማካይ 34 ኩንታል ምርት መገኘቱ መነቃቃት መፍጠሩን አስረድተዋል።

አምና በቆላማው የአፋር ክልልና በኦሮሚያ በተካሄደው የማላመድ ሥራ በ700 ሄክታር መሬት ላይ በመስኖ የለማው ከደጋ አካባቢ ያልተናነሰ ምርት በመስጠቱ ዘንድሮ በ3ሺህ 500 ሄክታር መሬት ላይ ተዘርቶ ምርቱ እየተሰበሰበ መሆኑንም ተናግረዋል።

በቆላ ስንዴ የመስኖ ልማት ላይ የታየውን ስኬት አጠናክሮ ለማስቀጠል መንግስት ከፍተኛ ቁርጠኝነት በማሳየቱምበቀጣዩ ዓመት በቆላማ የአገሪቱ አካባቢዎች 100 ሺህ ሄክታር ለማልማት መታቀዱን አቶ አደም አስታውቀዋል።

እየተገኘ ያለው ውጤት ልማቱን በየዓመቱ በማስፋት በሚቀጥሉት 5 ዓመታት ስንዴን ከውጭ ከማስገባት ለመላቀቅና ከተቻለም ወደ ውጭ መላክ የሚቻልበት ደረጃ ላይ ይደረሳል የሚል ተስፋ ማሳደሩን አስረድተዋል።

አቶ አደም እንዳሉት የወረር ግብርና ምርምር ማዕከል ለመስኖ ልማት አገልግሎት እንዲውሉ በምርምር ያስወጣቸውን ሰባት የዳቦና አንድ የፓስታና ማካሮኒ የቆላ ስንዴ ዝርያዎችን ወደ አርሶ አደሩ ለማዳረስ እየሰራ ነው።

"ዝርያዎቹም ጋምቦ፣ ሉሲ፣ ወረር፣ ፈንታሌ አንድ፣ ፈንታሌ ሁለት፣ አሚባራ አንድና አሚባራ ሁለት የሚል ስያሜ ተሰጥቷቸዋል" ብለዋል ።

የቆላ ስንዴ ዝርያዎቹ በጥቅምት ወር አጋማሽ ተዘርተው ከ80 እስከ 90 ቀናት ባለው ጊዜ ውስጥ ምርት መስጠት እንደሚችሉም ባለሙያው ተናግረዋል ።

የቆላ ስንዴው አሁን በመስኖ ከሚለማባቸው አካባቢዎች አንዳንዱ ስንዴን በእርዳታ ካልሆነ በስተቀር እንዴት እንደሚመረት በማያውቁ አርብቶ አደሮች አካባቢዎች መሆኑንም ተመራማሪው ተናግረዋል።

አቶ አህመድ መሀመድ በአፋር ክልል አሚባራ ወረዳ የባዳሃሞ ቀበሌ ነዋሪ ባለሀብት ሲሆኑ ከእዚህ ቀደም በአካባቢው ስንዴ በመስኖ ሲለማ አይተው አያውቁም ነበር።

አምና ከወረር ግብርና ምርምር ማዕከል የማዳበሪያ፣ የዘርና የባለሙያ እገዛ ተደርጎላቸው በ34 ሄክታር መሬት ላይ የቆላ ስንዴ በመስኖ በማልማት በሄክታር በአማካይ 37 ኩንታል ምርት ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

የአምናው ስኬት በፈጠረባቸው መነሳሳት ዘንድሮ በ260 ሄክታር መሬት ላይ ያለሙትን የቆላ ስንዴ በአሁኑ ወቅት በኮምባይነር በመሰብሰብ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

እየተሰበሰበ ካለው ምርት በመነሳት ዘንድሮ በሄክታር የሚያገኙት ምርት ከአምናው የተሻለ ይሆናል የሚል ተስፋ እንዳላቸውም አቶ አህመድ ገልፀዋል ።

በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን ፈንታሌ ወረዳ ፈቴሌዲ ቀበሌ ነዋሪዎች በበኩላቸው እንዳሉት በታሪካቸው የቆላ ስንዴን በመስኖ ሲለማ ሲያዩ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ።

ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ አብዶ ኒኒ በሰጡት አስተያየት ዘንድሮ በግብርና ምርምር ድጋፍ 1 ነጥብ 5 ሄክታር መሬት በቆላ ስንዴ እንዲሸፈን አድርገዋል።

በማሳ ላይ እየታየ ያለው ሰብል ተስፋ ሰጪ መሆኑን ገልጸው ልማቱን የበለጠ ለማጠናከር ሁሉንም የመንግስት አካላት ትኩረት እንዲሰጡበት ጠይቀዋል ።

አቶ ሙሳ ዱቤ የተባሉት ነዋሪ በበኩላቸው በ1 ሄክታር መሬት ላይ ስንዴን በመስኖ የማልማት ሥራ ማካሄድ እንደጀመሩ ገልጸው የደረሰው ሰብል ወፍ እያጠፋውና ከአቅማቸው በላይ እየሆነ በመሆኑ ለወደፊት መፍትሄ እንዲፈለግ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም