እነ ሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው ያቀረቡት የክስ መቃወሚያ ውድቅ ሆነ

192

አዲስ አበባ የካቲት 26/2011 የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት እነ ሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው ያቀረቡትን የክስ መቃወሚያ ውድቅ አደረገ።

በእነ ሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው የክስ መዝገብ የአክሰስ ሪልስቴት መስራችና ባለቤት የሆኑትን አቶ ኤርሚያስ አመልጋን ጨምሮ ስምንት ሰዎች በዐቃቤ ሕግ የቀረበባቸውን ክስ እንዳልፈጸሙ ለፍርድ ቤት አስረድተዋል።

ዐቃቤ ሕግ በቀድሞ የብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘውን ጨምሮ ስምንት ሰዎች ላይ በኢምፔሪያልና በሪቬራ ሆቴሎች እንዲሁም በፕላስቲክ ማምረቻ ፋብሪካ ግዢና ሽያጭ ሒደት ላይ ክስ መመስረቱ ይታወቃል።

በክስ መዝገቡ ሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው፣ ኮሎኔል ሙሉ ወልደገብርኤል፣ ብርጋዴር ጄኔራል በርሃ በየነ፣ አቶ ዓለም ፍጹም፣ ሌተናል ኮሎኔል አስመረት ኪዳኔ፣ ሌተናል ኮሎኔል ግርማ መንዘርጊያ፣ ሻምበል አግዘው አልታዬና አቶ ኤርሚያስ  አመልጋ ይገኙበታል።

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 15ኛ ወንጀል ችሎት ዛሬ ጠዋት በዋለው ችሎት ተከሳሾች ባቀረቡት የክስ መቃወሚያ ላይ የዐቃቤ ሕግ ምላሽን መርምሮ ብይን ሰጥቷል።

አንደኛ ተከሳሽ ሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው ያቀረቡት የክስ መቃወሚያ በዐቃቤ ሕግ የክስ መመስረቻ ጽሑፍ ላይ 'ስልጣንን ያለ አግባብ መጠቀም' የሚለው ክስ በግልጽ እንዲቀርብ ያቀረቡትን መቃወሚያ ፍርድ ቤቱ 'የዐቃቤ ሕግ ክስ በግልጽ የስልጣንን ምንጭ በዝርዝር ያስቀመጠነ ነው' ሲል ውድቅ አድርጎታል።

በኢምፔሪያልና በሪቬራ ሆቴሎች እንዲሁም በፕላስቲክ ማምረቻ ፋብሪካ ግዢ ላይ በአገሪቱ ሆቴልና ፋብሪካ ገንብቶ የሚሸጥ አካል ባለመኖሩ ጨረታ ማካሄድ አልተቻለም ተብሎ የቀረበው የክስ መቃወሚያ ፍርድ ቤቱ ወደፊት በክርክር ሂደት የሚታይ እንደሆነ በመግለጽ የክስ መቃወሚያውን ውድቅ አድርጓል።

በተመሳሳይ በሆቴልና በፕላስቲክ ፋብሪካ ግዢ ላይ የኮርፖሬሽኑን ዓላማ ለማስፈጸም የተካሄደ ነው ተብሎ የቀረበው መቃወሚያ ወደፊት ዝርዝር ማስረጃዎች ሲሰሙ የሚታይ እንደሆነም ፍርድ ቤቱ አስታውቋል።

11ኛ ተከሳሽ አቶ ኤርሚያስ ጠቅል አመልጋ ባቀረቡት የክስ መቃወሚያ ''ኤምፔሪያል ሆቴል አሁን ባለው የገበያ ዋጋ ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ ነው ተብሎ መቅረቡ የተጋነነ ዋጋ ነው ሊባል አይገባም'' ብለዋል።

ፍርድ ቤቱ በዐቃቤ ሕግ የቀረበው ክስ ሆቴሉ በተሸጠበት ወቅት የነበረ ዋጋ ሲሆን በዚህ ክስ ላይ ምላሽ የሚሰጠው ማስረጃዎች ከተሰሙ በኋላ  እንደሆነም አስታውቋል።

ተከሳሾቹ በዐቃቤ ሕግ የቀረበባቸውን የወንጀል ድርጊት እንዳልፈጸሙና ወንጀለኛም እንዳልሆኑ የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጥተዋል።

ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ ተከሳሾቹ 'ወንጀሉን አልፈጸምንም' ሲሉ የሰጡት የክህደት ቃል በመሆኑ ለፍርድ ቤቱ የቀረበው የክስ ማስረጃዎች እንዲመረመሩና ለምስክሮች መጥሪያ እንዲላክ ጠይቋል።

ፍርድ ቤቱ ዐቃቤ ሕግ በማስረጃነት ያቀረባቸውን 12 የሰው ምስክሮች በተከታታይ ለማድመጥ ለመጋቢት 30 ቀን 2011 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም