ብሄራዊ ፓርኩን ከአደጋ ለመጠበቅ እንሰራለን ---የፍትህ አካላት

56

ጎባ የካቲት 26/2011 በባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ብዝሃ ህይወት ላይ እየደረሰ የሚገኘውን ውድመት ለመታደግ የድርሻቸውን እንደሚሰሩ የፍትህ አካላት ገለጹ።

የፓርኩን ችግሮች ለማቃለል በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ በጎባ ከተማ ተካሒዷል።

ከተሳታፊዎች መካከልም በባሌ ዞን ፖሊስ መምሪያ የወንጀል ምርመራ ዲቪዥን አስተባባሪ ምክትል ኮማንደር ተስፋዬ ከበደ እንደተናገሩት በፓርኩ ዙሪያ የሚኖረው ህዝብ ቁጥር መጨመርና የእርሻ  መሬት መስፋፋት የፓርኩን ህልውና እየተፈታተኑት ነው፡፡

በየደረጃው የሚገኙ የፍትህ አካላትም በፓርኩ ላይ ጥፋት በማድረስ ለህግ የሚቀርቡ አጥፊዎች ላይ የሚወስዱት የህግ እርምጃ ወጥነት ስለሌለው ችግሩ እንዲባባስ ምክንያት መሆኑን አስረድተዋል።

“የምክክር መድረክ መዘገጀቱ በፓርኩ ላይ እየደረሰ የሚገኘውን ተግዳሮት በመገንዘብ በቅንጅት ለመስራት እድል ይፈጥራል” ብለዋል።

የባሌ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ አቶ መለሰ አብረሃም በበኩላቸው በአካባቢና በደን ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመከላከል የሚረዱ ህጎችንና መመሪያዎችን በመተግበር ረገድ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለመሙላት የመድረኩ መዘጋጀት ጉልህ ሚና አለው።

በፓርኩ ላይ የተጋረጠውን አደጋ ለመታደግ በአጥፊዎች ላይ ከሚወሰደው እርምጃ  በተጓዳኝ በየደረጃው የሚገኘው አመራር የአካባቢውን ነዋሪዎች የግንዛቤና የአመለካከት ክፍተት ለመሙላት በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

“ማህበረሰቡ ከፓርኩ በኢኮ-ቱሪዝምና ተያያዥ ጉዳዮች የሚገኘውን ጥቅም እንዲጋራና ባለቤትነቱን እንዲያጎለብት በማድረግ እየደረሰ የሚገኘውን ጫና ለመቀነስ ሊሰራ ይገባል” ያሉት ደግሞ ሌላዋ የመድረኩ ተሳታፊ ወይዘሮ አስቴር ግርማ ናቸው፡፡

የባሌ ዞን የአካባቢ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን ተወካይ አቶ አሰፋ ሁንዴ በበኩላቸው “በፓርኩ በሚገኘው ብዝሐ ህይወት ላይ እየደረሰ ያለው ውድመት ፓርኩን አደጋ ላይ እንዲወድቅ እያደረገው ነው”ብለዋል።

በፓርኩ ዙሪያ የሚኖረው ህዝብ ቁጥር መጨመር፣ የእርሻ መሬት መስፋፋት፣ የደን ምንጣሮ፣የእሳት ቃጠሎ፣ ልቅ ግጦሽና መሰል ችግሮች መስፋፋት ለፓርኩ አደጋ ምክንያት እንደሆነ ተናግረዋል።

በተለይ ሰሞኑን በፓርኩ ክልል ውስጥ የተከሰተው የእሳት ቃጠሎ በዋናው የፓርኩ ጥብቅ ደን ላይ ጉዳት ባያደርስም 200 ሄክታር በሚሆን መሬት ላይ በነበረው ቁጥቋጦና ሌሎች ብዝሐ ህይወቶች ላይ አደጋ ማድረሱን በማሳያነት አቅርበዋል፡፡

ቃጠሎው የከፋ ጉዳት ሳያስከትል በህብረተሰቡ ተሳትፎና በሀገር መከላከያ ሰራዊት ጥረት ለመቆጣጠር መቻሉን የጠቆሙት ተወካዩ በቀጣይነት ካልተሰረበት በተደጋጋሚ የሚነሳው የእሳት ቃጠሎ የፓርኩን ህልውና ጥያቄ ውስጥ እንደሚያስገባ ተናግረዋል፡፡

ፓርኮቹን ከውድመት ለመታደግ ባለስልጣኑ ከፍትህ አካላትና በየደረጃው ከሚገኙ ሌሎች ባለድርሻዎች ጋር የንቅናቄ መድረኮችን ማካሄዱ የህግ የበላይነትን በማረጋገጥ በኩል ይታዩ የነበሩ ክፍተቶችን ለመሙላት እንደሚያግዝ  አስረድተዋል፡፡

ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣትም የአካባቢውን ማህበረሰብ ህይወት ለመለወጥ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ከተለያዩ መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር በትኩረት እየተሰራበት እንደሆነ ተናግረዋል።

በፋርም አፍሪካ ኤስ ኦ ኤስ ድርጅት የባሌ ፕሮጄክት ተወካይ አቶ ስዩም ከበደ በበኩላቸው እንደተናገሩት ድርጅቱ ፓርኩን ከአደጋ ለመከላከል ከመንግስት ጎን በመሆን የህብረተሰቡን ግንዛቤ በማሳደግና ሌሎች ድጋፎችን በማድረግ  የበኩሉን ድጋፍ እያደረገ ይገኛል።

“በተለይም በፓርኩ አዋሳኝ የሚገኙ ነዋሪዎችን ህይወት ለመለወጥ የተለያዩ የገቢ ማስገኛ የፕሮጀክት አማራጮችን በመንደፍ በፓርኩ ላይ እየደረሰ የሚገኘውን ተጽእኖ ለመቀነስ በትኩረት እየሰራ ይገኛል”ብለዋል።

የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በተባበሩት መንግስታት የትምህርት የሳይንስና የባህል ተቋም /ዩኔስኮ/ በጊዜያዊ መዝገብ ላይ የተመዘገበ የተለያዩ ብርቅዬ የዱር አራዊትና አእዋፍ መገኛ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም