የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 2ኛ ዙር ውድድር የሚጀመርበት ጊዜ በአንድ ሳምንት ተራዘመ

97

አዲስ አበባ የካቲት 26/2011 የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የፕሪሚየር ሊጉ 2ኛ ዙር ውድድር የሚጀመርበት ጊዜ በአንድ ሳምንት መራዘሙን አስታወቀ።

ከዚህ በፊት የፕሪሚየር ሊጉ 2ኛ ዙር መርሃ ግብር መጋቢት 1 ቀን 2011 ዓ.ም እንደሚጀመር ተገልጾ ነበር።

አሁን ማስተካከያ ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ የፕሪሚየር ሊጉ 2ኛ ዙር ውድድር ከተያዘለት የጨዋታ መርሃ ግብር አንድ ሳምንት ዘግይቶ እንዲጀመር ፌዴሬሽኑ ወስኗል። 

በዚሁ መሰረት መጋቢት 1 ቀን 2011 ዓ.ም ባህርዳር ከተማ ከቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከሀዋሳ ከተማ፣ ወላይታ ዲቻ ከስሑል ሽረ፣ መከላከያ ከደቡብ ፖሊስና ድሬዳዋ ከተማ ከኢትዮጵያ ቡና ሊያደርጓቸው የነበሩ ጨዋታዎች መጋቢት 8 ቀን 2011 ዓ.ም የሚካሄዱ ይሆናል።

መጋቢት 8 ቀን 2011 ዓ.ም ጅማ አባ ጅፋር ከአዳማ ከተማ፣ ደደቢት ከመቐለ ሰብዓ እንደርታና ፋሲል ከተማ ከሲዳማ ቡና የሚያደርጓቸው ጨዋታዎች በወጣላቸው መርሃ ግብር መሰረት እንደሚካሄዱ ታውቋል።

የመጀመሪያ ዙር የፕሪሚየር ሊጉ ውድድር የካቲት 21 ቀን 2011 ዓ.ም መጠናቀቁ ያታወሳል።

የፕሪሚየር ሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ መቐለ ሰብዓ እንደርታ በ35 ነጥብ ሲመራ፣ ሲዳማ ቡና በ30 ነጥብ 2ኛ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ በ26 ነጥብ 3ኛ ደረጃን ይዘዋል።

ደቡብ ፖሊስ፣ ስሑል ሽረና ደደቢት በቅደም ተከተል ከ14ኛ እስከ 16ኛ ያለውን ደረጃ በመያዝ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛሉ።

የፕሪሚየር ሊጉን ኮከብ ግብ አግቢነት የመከላከያው ምንይሉ ወንድሙና የመቐለ ሰብዓ እንደርታው አማኑኤል ገብረሚካኤል በተመሳሳይ 11 ግቦች ሲመሩ የሲዳማ ቡናው አዲስ ግደይ በ10 ግቦች ይከተላል።

በሌላ በኩል ህዳር 3 ቀን 2011 ዓ.ም የተጀመረው የ2011 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ጥሎ ማለፍ ውድድር ከመጋቢት 7 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ በሚካሄዱ ጨዋታዎች እንደሚቀጥል ፌዴሬሽኑ ገልጾ ነበር።

በወጣው መርሃ ግብር መሰረት መጋቢት 7 ቀን 2011 ዓ.ም በአዲስ አበባ ስታዲየም ኢትዮጵያ ቡና ከስሑል ሽረ የሩብ ፍጻሜ ጨዋታቸውን ማድረግ የነበረባቸው ቢሆንም ጨዋታው ወደ ግንቦት 1 ቀን 2011 ዓ.ም መዘዋወሩ ተጠቅሷል።

ሌሎች ቀሪ የጥሎ ማለፉ ጨዋታዎች ቀንና ቦታ ወደ ፊት እንደሚገልጽ ፌዴሬሽኑ አስታውቋል።

የጥሎ ማለፍ ውድድር አሸናፊው ክለብ በ2012 ዓ.ም ኢትዮጵያን በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ በመወከል ይሳተፋል።

መከላከያ የ2010 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች የጥሎ ማለፍ ውድድር አሸናፊ እንደነበር ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም