ጃፓን ለአፍሪካ ለመምህራንን የአቅም ግንባታ የሚውል የ500 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ድጋፍ አደረገች

63

አዲስ አበባ የካቲት 26/2011 ጃፓን ለአፍሪካውያን መምህራን የአቅም ግንባታ ስልጠና ለመስጠት የሚያስችል የ500 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ድጋፍ አደረገች።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፥ የሳይንስና የባህል ተቋም (ዩኔስኮ) በአፍሪካ የሚሰጠውን ድጋፍ በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ዳይሱኪ ማታሱንጋና የዩኔስኮ የአፍሪካ አለም አቀፍ አቅም ግንባታ ኢኒስትቲዩት ዳይሬክተር ዶክተር ዮሚኮ ዩኮ በዛሬው እለት ተፈራርመዋል።

ድጋፉ የአፍሪካ መምህራን በተማሪዎቻቸው ውስጥ የሰላምን አስፈላጊነት በማስረጽ ፅንፈኝነትን ለመከላክል ለሚተገበር ፕሮጀክት እንደሚውል ተገልጿል።

በዚህ ጊዜ የዩኔስኮ የአፍሪካ አለም አቀፍ አቅም ግንባታ ኢኒስትቲዩት ዳይሬክተር ዶክተር ዮሚኮ ዩኮ እንደገለጹት፤ ድጋፉ በአፍሪካ ሰላምና ልማትን ለማስፈን በሚደረገው ጥረት ከመምህራን ጋር ውጤታማ ስራ ለመስራት ያስችላል።

ለዚህም በጃፓን መንግስት ድጋፍ እአአ በ2017 በምስራቅ አፍሪካና በ2018 በሳህል ቀጣና "የመምህራን ስልጠናና ልማት ለሰላም ግንባታ" በሚል ዩኔስኮ ሲተገብረው የነበረው ፕሮጀክት ማሳያ መሆኑን አስታውሰዋል።

አሁን የተገኘው ድጋፍ ከዚህ በፊት የተገኙ ልምድና ተሞክሮዎችን መነሻ በማድረግ "በአፍሪካ ሰላምን ለማስፈንና አደጋን የመቋቋም  ፕሮጀክት" ለመተግበር ይውላል።

''ፕሮጀክቱ በ12 የአፍሪካ አገሮች ሶስት ሺህ የሚጠጉ አሰልጣኝ መምህራንን በማሰልጠን ከ120 ሺህ በላይ ሌሎች መምህራንንና ለሰላም ከፍተኛ ሚና የሚጫወቱ ተማሪዎችን ተደራሽ ለማድረግ ያስችላል'' ብለዋል።

በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ዳይሱኪ ማታሱንጋና በበኩላቸው በመምህራን ልማት ላይ በትኩረት መስራት መምህራን በማህበረሰቡ ውስጥ ሰላምና መረጋጋት እንዲያሰፍኑ ለማስቻል የሚደረገውን ጥረት እንደሚደግፍ ገልጸዋል።

ከዚህ ቀደም በነበሩት ፕሮጀክቶች የተገኘው አፈፃፀም መልካም ማሳያ እንደሆነ ጠቅሰው ያለፉት ፕሮጀክቶቹ ውጤታማ መሆናቸውን ተከትሎ የጃፓን መንግስት ድጋፉን ለማድረግ እንደወሰነ ጠቅሰዋል።

በአሁኑ ወቅት በምስራቅ አፍሪካ በተለይም በኢትዮጵያና በኤርትራ የተፈጠረው ሰላም እና በጥሩ መንገድ እየተጓዘ ያለውን የደቡብ ሱዳን የሰላም ስምምነት ለመደገፍም ያስችላል ሲሉ አምባሳደሩ አክለዋል።

ፕሮጀክቱ በዋናነት በአልጄሪያ፣ በቡርኪና ፋሶ፣ በካሜሮን፣ በመካለኛው አፍሪካ፣ በቻድ፣ ኤርትራ፣ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ሊቢያ፣ ማሊ፣ ሞርታኒያ፣ ኒጀር፣ ናይጄሪያ፣ ሴኔጋል፣ ሶማሊያ፣ ደቡብ ሱዳንና ዩጋንዳ ይተገበራል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም