በበሰቃ ሀይቅ ዳርቻ በ80 ሚሊዮን ዶላር የተገነባው ልዩ መዝናኛ ስፍራ አገልግሎት ሳይጀምር እየፈረሰ ነው

63

አዳማ የካቲት 26/2011 በበሰቃ ሀይቅ ዳርቻ በ80 ሚሊዮን ዶላር ወጪ በልዩ የኪነ ህንፃ ጥበብ እንደተገነባ የሚነገርለት ልዩ የመዝናኛ ስፍራ አገልግሎት መስጠት ሳይጀምር ለስምንት ዓመታት ባለቤት አልባ ሆኖ በመቆየቱ መልሶ እየፈረሰ ነው ተባለ።

ልዩ የመዝናኛ ስፍራው ከመተሀራ ከተማ በሦስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በ143 ሔክታር መሬት ተከልሎ የተገነባ በመሆኑ ከሩቁ ለየት ብሎ ይታያል ።

ከርቀት ምንድነው ብለህ ብትጠይቅ ግን በውጭ አገር ሰዎች የተገነባ ልዩ የመዝናኛ ስፍራ ነው ሲባል የሰማ እንጂ፤ በእርግጠኝነት ዝርዝር መረጃ ያለው የከተማው ነዋሪ ማግኘት አስቸጋሪ ነው ።

ስለሁኔታው ለማወቅ ጉጉት ያደረበት የኢዜአ የጋዜጠኞች ቡድን ከፈንታሌ ወረዳ ኢንቨስትመንትና ከወረዳው የኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤት ሁለት ባለሙያዎችን በመያዝ ወደ ቦታው ያቀና ሲሆን፣ ግንባታው የሚደነቅ ብክነቱ ግን የሚያሳዝን መሆኑን በዘገባው አካትቶታል ።

ወደቦታው ለመግባት ሜዳ ሜዳውን እየመረጡና ከፕሮሶፒስ እሾሃማ መጤ አረም ጋር እየታገሉ እንጂ፤ መኪና ሲመላለስበት የነበረው የገጠር መንገድ አገልግሎት ሳይሰጥ ረጅም ጊዜ በመቆየቱ ተበላሽቷል ።

በቦታው በበሰቃ ሀይቅ ዳርቻ እየዋኙ ከሚጫወቱ ጥቂት የአርብቶ አደር ህፃናት ልጆች በስተቀር አንድም የጥበቃ ሰራተኛ አልነበረም ።

የፈንታሌ ወረዳ ኢንቨስትመንት ጽህፈት ቤት ባለሙያ አቶ ከማል ዑመር እንደሚሉት ግንባታው በ80 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ከ1999 እስከ 2003 በነበረው ጊዜ ውስጥ የተካሄደ ሲሆን፣ ባለቤቱም ሶል ጆኦት ሳዑዲ አሜሪካን ኢንቨስትመንት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ በሚል የተመዘገበ ነው ።

የሳዑዲ አረቢያ ተወላጅ የሆኑት የኩባንያው ባለቤት በ2003 የበሰቃ ሀይቅ የውሃ መጠኑ ጨምሮ ወደ መዝናኛ ስፍራው በመግባት በግንባታው ላይ ጉዳት በማድረሱ ተበሳጭተው አካባቢውን ለቀው በመሄዳቸው ግንባታው ሙሉ በሙሉ ሳይጠናቀቅና አገልግሎት መስጠት ሳይጀምር መቅረቱን ባለሙያው ተናግረዋል።

በጊዜ ሒደት ባለሃብቱ እዚያው አገራቸው ላይ እንደሞቱ የተሰማ ሲሆን፣ ህጋዊ ወራሾች የሆኑ ቤተሰቦቻቸው ስራውን ለማስቀጠል  ፍላጎት እንዳላቸው ከአንድ ወር በፊት ለመንግስት አሳውቀው እንደተፈቀደላችው አቶ ከማል አስረድተዋል።

ግንባታው ከመቋረጡ በፊት አርብቶ አደሮችን ጨምሮ 300 ለሚሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎች ስራ የፈጠረ ነበር ተብሏል።

ወጣቱ ዓሳ አጥማጅ ዴቪድ ብርሃኑ በመዝናኛ ስፍራው የሚገኘው አንዱ ማማ መኖሪያው አድርጎ እየተጠቀመበት መሆኑን ይገልፃል።

ወጣት ዴቪድ ተወልዶ ያደገው በመተሃራ ከተማ ቀበሌ 01 ነበር።አሁን ግን ወደ ከተማ የሚወጣው ያጠመደውን የዓሳ ምርት ለመሸጥ ብቻ ሆኗል።

''ባለሃብቱ ጥሩ ሰው ነበሩ ። ለበርካታ ወጣት አርብቶ አደሮች የስራ እድል በመፍጠር ተጠቃሚ አድርገው ነበር ። አካባቢውን ለቀው ከሔዱ በኋላ ብዙ ንብረት ተዘርፏል ። ግንባታው አገልግሎት ሳይጀምር መልሶ እየፈረሰ በመሆኑ  ዘላቂ መፍትሄ ቢበጅለት መልካም ነው'' የሚል አስተያየት ሰጥቷል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም