መንግስት በፌደራሊዝም ስርዓቱ አፈፃፀም ላይ የታዩ ችግሮችን ለመፍታት እየሄደበት ያለው ርቀት ውጤት ይኖረዋል-ምሁራን

71
አዲስ አበባ ግንቦት 22/2010 መንግስት በፌደራሊዝም ስርዓቱ አፈፃፀም ላይ የታዩ ችግሮችን ለመፍታት እየሄደበት ያለው ርቀት ውጤት እንደሚያመጣ ያላቸውን እምነት  ምሁራን ገለፁ። አገሪቷ ላለፉት አመታት በፌዴራሊዝም ስርዓቱ ያመጣቻቸው በርካታ ስር ነቀል ለውጦች መኖራቸውንም በሰመራ ዩኒቨርሲቲ የስነዜጋና ስነ ምግባር መምህራን ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ተናግረዋል። ከአስተያየት ሰጭዎች መካከል መምህር ግርማይ አለማየሁ « ሰዎች በማንነታቸው ሲያፍሩ፣ ስም ሲቀይሩ፣ በሌላ ስም ሲጠሩ፣  በሌላ ቋንቋ ለመናገር እሚያፍርበት፣ እሚሸማቀቅበት ዘመን ነበር ፤አሁን  በማንነትህ በቋንቋህ መኩራት አንድ ትልቅ ውጤት ነው፤ እነዚህ በቋንቋህ መጠቀም፣ በቋንቋህ መዳኘት፣ መማር የፌዴራሊዝም ውጤቶች ናቸው፤ እነዚህ ይቀጥላሉ እንጂ ከነዚህ ወደኋላ መመለስ የሚቻል አይመስለኝም» ነው ያሉት። "ክልሎች እራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩና ስልጣን ወደታች ወርዶ የራሳቸውን ስራ በአግባቡ እንዲሰሩ መደረጉ አንዱ ውጤት ነው። ከትምህርትና ከጤና ግብዓት አንፃርም ብዙ ለውጦች አሉ። ክልሎች ከክልሎች እርስ በርሳቸው በመንገድ ተገናኝተዋል፤ ዩኒቨርስቲዎች በየቦታው ተከፍተዋል፤ ይሄ መልካም ነገር መሆኑን የገለጹት ደግሞ መምህር ብስራት ተክለስላሴ ናቸው፡፡ እንደ ምሁራኑ ገለጻ ምንም እንኳን ስርዓቱ የሚታይና ዘርፈ ብዙ ውጤቶችን ቢያስመዘግብም በአተገባበር እና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ጨምሮ በሙስናና በሌሎች የስርዓቱ ተግዳሮቶች ሳቢያ የታሰበውን ያህል ጎልቶ አልወጣም። በመሆኑም አሁንም መንግስት በያዘው እንቅስቃሴ በነዚህ ችግሮች ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ የሚታይ ለውጥ መምጣት አለበት ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። "እየኖርንበት ያለውን ችግር ከመለየት ጀምሮ እንዴት ይፈታሉ? ግልጽ የሆነ ሌብነት አለ፤ ሌብነት አገር ሊያፈርስ ደርሷል፤ እዚህ ላይ ትኩረት መደረግ እንዳለበት  መምህር ሄኖክ ተስፋዬ ገልጸዋል ። መምህር ግርማይ አለማየሁ የተባሉ አስተያየት ሰጭ "ሌብነት በዛ፤ መልካም አስተዳደር ጠፋ፤ ጉዳይ ትፈፅማለህ እንዴ? ጉዳይ እኮ አይፈፀምም፤ ሌባው ሙሰኛው እራሱ ሙስናን እንቃወም እያለ እየቀለደብን ነው"፤ ሌባንና ሙስናን የሚከለክል ዘዴ መቀየስ እንዳለበት ነው የተናገሩት ፡፡ መንግስት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንደ አገር የታዩ ችግሮችን ለይቶ ለመፍታት እያደረገ ያለው ጥረት ወደፊት ጥሩ ውጤት የሚያስገኝና በህዝቡ ላይ የአመለካከት ለውጥ እያመጣ ያለ ተግባር መሆኑንምምሁራኑ ገልጸዋል፡፡ የፌዴራሊዝም ስርዓቱ በርካታ ለውጦችን ቢያስመዘግብም "አብሮነትንና ኢትዮጵያዊነትን ከማጠንከር አኳያ ክፍተት ነበረበት" ያሉት ምሁራኑ፤ በተለይ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከዚህ አንፃር የሰሩት ስራ ትልቅ ውጤት ያለው ነው ሲሉም ገልፀዋል። በቀጣይም አሁን የተያዙት አቅጣጫዎች ተቋማዊ ሆነው በተግባር የሚታዩ መሆን ይጠበቅባቸዋልም ብለዋል። መምህር ግርማይ አለማየሁ"አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትራችን ክቡር ዶክተር አብይ አህመድ  ከቀን አንድ ጀምሮ ያለማቋረጥ በየቦታው በየአካባቢው የሚናገሯቸው ንግግሮች በኢትዮጵያዊነት ካልሆነ መቀጠል አንችልም የሚለው ነገር ማንም ሰው ላይ ተስፋ ያሳደረ ነው፤ እነዚህ ንግግሮች፣  አስተያየቶች  ካሉ መመሪያዎችና ፖሊሲዎች ጋር ተጣጥመው በትምህርትም ሆነ በሌላ ዘርፍ መግባት አለባቸው "ብለዋል፡፡ መንግስት አገሪቷን ለገጠሟት ችግሮች  መፍትሔ ለማምጣት ሰፊ ድርጅታዊ ግምገማዎችን ካደረገ  በኋላ ዘርፈ ብዙ የለውጥ እርምጃዎችን ወስዶ ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ገብቷል። በዚህም ከተደረጉት የለውጥ እርምጃዎች ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠርና የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት የሚያስችሉ ተጨባጭ እርምጃዎች እየተወሰዱ ናቸው። እነዚህ የለውጥ እርምጃዎች ለፌዴራሊዝም ስርዓቱ ቀጣይነት የጎላ ሚና እንደሚኖራቸው ምሁራኑ ተናግረዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም