በተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራ ላይ የሚከናወኑ ምርምሮች አሳታፊ ሊሆኑ እንደሚገባ ተጠቆመ

98

አዳማ  የካቲት 25/2011 በተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራ ላይ የሚከናወኑ ችግር ፈቺ ምርምሮች አሳታፊ ሊሆኑ እንደሚገባ የአካባቢ፣ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን አስታወቀ።  

የኢትዮጵያ የአካባቢና የደን ምርምር ኢንስቲትዩት ያዘጋጀው 5ኛው ብሔራዊ የምርምር ፕሮጀክት ግምገማ አውደ ጥናት ትናንት በአዳማ ከተማ ተጀምሯል።

በዚህ ወቅት የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ፕሮፌሰር ፍቃዱ በየነ እንዳስታወቁት ሀገሪቱ በዘላቂ የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ረገድ ያልተሻገረቻቸው ተግዳራቶች አሉ።

በቅርቡ ከዓለም የምግብ ድርጅት ጋር በተደረገው ሀገራዊ የደን ሀብት ቆጠራ የደን ሀብቱ በከፍተኛ ችግር ውስጥ እንዳለ መረጋገጡን ለአብነት ጠቅሰዋል።

"የደን ሀብት ውድመት የሚያስከትለው ተጽዕኖ ሰፊ ነው" ያሉት ፕሮፌሰሩ በተለይ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሥነ ምህዳራዊ ጠቀሜታ ያላቸው እጽዋቶች እስከመጨረሻው እንዲጠፉ የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህንን ችግር ለመቋቋም የሚያስችል አቅም መገንባት እንደሚያስፈልግ ጠቁመው በዘርፉ ሳይንሳዊ ጥናትና ምርምርን በቅንጅት መስራት እንደሚጠይቅ አመልክተዋል።

ከአገር ውስጥና ከውጭ ሀገር ካሉ የምርምር ተቋማት፣ ከዩኒቨርሲቲዎች፣ ከግል ባለሀብቶች፣ ከማህበራትና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር ተቀራርቦ መስራት ወሳኝ መሆኑንም አስታውቀዋል።

"ይህን ማድረግ ከተቻለ ሀገሪቷ ወደ ውጭ ሀገር መላክ ሲኖርባት በዓመት ከ200 ሚሊዮን ዶላር በላይ እያወጣች የምታስገባውን የደን ውጤት በሀገር ውስጥ ምርት መተካት ይቻላል" ብለዋል ፕሮፌሰር ፍቃዱ።

በተጨማሪም በየዓመቱ ከተፋሰሶች ሊታጠብ የሚችለውን በቢሊዮን ቶን የሚለካ አፈር ወደ ወንዞች፣ ሐይቆችና ግድቦች እንዳይገባ መከላከል እንደሚቻል አመልክተዋል።

በአካባቢና በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ የሚካሄዱ ምርምሮችን ኮሚሽኑ እደሚያበረታታና ወደመሬት እንዲወርዱ በቅርበት እንደሚደግፍም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የአካባቢና የደን ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አብዮት ብረሃኑ በበኩላቸው ኢኒስቲቲይቱ በአሁኑ ወቅት በአካባቢ፣ በደን ጥበቃ፣ በዘርና በእንጨት ቴክኖሎጂ ዙሪያ በርካታ የምርምር ሥራዎችን ውጤታማ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

" የአካባቢ መራቆትና የአየር ንብረት ለውጥ እያስከተለ ያለውን ጉዳት እንዲሁም የብርቅዬ ብዝሃ ሕይወት መገኛ የሆኑ ደኖች ላይ እየደረሰ ያለውን ጥፋት ለመግታት የመረጃና የቴክኖሎጂ እቅርቦትን ለተጠቃሚው ተደራሽ ለማድረግም ጥረት እየተደረገ  ነው " ብለዋል።

ከዚህ በፊት ወደ ሙከራ የገቡ፣ የተጠናቀቁና አዲስ የተቀረጹ 149 የምርምር ፕሮጀክቶች በአውደ ጥናቱ እንደሚገመገሙ ያመለከቱት ደግሞ የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አጌና አንጁሎ ናቸው።

በምርምር የተገኙ ውጤቶችና ያጋጠሙ ችግሮች፣ የፕሮጀክቶቹ አዋጭነትና ፋይዳ ላይ የጋራ መግባባት ለመፍጠር ታስቦ መድረኩ መዘጋጀቱንም ጠቁመዋል።

ለመድረኩ ከቀረቡት የምርምር ፕሮጀክቶች መካከል የደን ሃብት አጠቃቀም፣ የዛፍ ዘር ቴክኖሎጂ፣ የአካባቢ ብክለት አያያዝና የአየር ንብረት ለውጥ የሚሉት እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።

ለአራት ቀናት በተዘጋጀው በዚሁ አውደ ጥናት ላይ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና፣ የአርብቶ አደርና የተፈጥሮ ሀብት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት፣ ከመላ ሀገሪቱ የተውጣጡ የምርምር ተቋማት የሥራ ኃላፊዎችና ተመራማሪዎች እንዲሁም የዩኒቨርሲቲ ምሁራን ተሳትፈዋል።

ኢንስቲትዩቱ ባለፉት 40 ዓመታት በዛፍ ዘር ቴክኖሎጂ ብቻ 308 ሺህ ኪሎ ግራም ዘር ለተጠቃሚዎች ማሰራጨቱ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም