ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ከሶማሊያ ፕሬዚዳንት ጋር ተወያዩ

705

አዲስ አበባ የካቲት 26/2011 ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከሶማሊያ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት መሐመድ አብዱላሂ መሐመድ ጋር በቀጣናው ሰላምና ደህንነት እንዲሁም በኢኮኖሚያዊ ትስስር ላይ ውይይት አደረጉ።

የሶማሊያ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት መሐመድ አብዱላሂ ይፋዊ የስራ ጉብኝት ለማድረግ ዛሬ አዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች አቀባበል አድርገውላቸዋል።

ሁለቱ መሪዎች በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በቀጣናው ሰላምና ደህንነት ጉዳዮች ላይ ረዘም ያለ ውይይት አካሂደዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ከውይይቱ በኋላ እንደገለጹት፤ ሁለቱ መሪዎች ከዚህ በፊት የተጀመሩ የሁለትዮሽና ቀጣናዊ ግንኙነቶችን ለማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ መክረዋል።

ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ጋር ወደብ ማልማት መጠቀም በምትችልበትንና በአጠቃላይ በምጣኔ ሀብት ትስስር ዙሪያ መሪዎቹ ሰፊ ምክክር ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

እንዲሁም ከሶማሊላንድ አስተዳደር ጋር ባለው ግንኙነት ላይ ውይይት ማካሄዳቸውን አቶ ንጉሱ ተናግረዋል።

ሁለቱ መሪዎች በሶማሊያና በኬንያ መካከል ያለውን ግንኙነት የተሻለ ደረጃ ላይ ለማድረስ በሚቻልበት ጉዳይ ላይ መምከራቸውን አቶ ንጉሱ ገልጸዋል።

የቀጣናውን ሰላምና ደህንነት በማስጠበቅ በጎረቤት አገሮች መካከል ያለውን ችግር በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ሁለቱ መሪዎች ውይይት ያደረጉበት ነጥብ እንደነበረም አስረድተዋል።

የቀጠናውን ምጣኔ ሀብታዊ ትስስር ለማጎልበት የኢትዮጵያና የሶማሊያ ግንኙነት ወሳኝ እንደሆነ የገለጹት አቶ ንጉሱ፤ የሁለቱ አገሮችን መልካም ግንኙነት በማጎልበት የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን ለማለፍ በጋራ ለመስራት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ መሪዎቹ በሰፊው መምከራቸውን አቶ ንጉሱ ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ ቀን ጀምሮ ከኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ፣ ከኤርትራ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂና ከደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር ማያርዲት ጋር በቀጣናው ሰላምና ደህንነት እንዲሁም የሁለትዮሽ ግንኙነቾችን ለማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ውይይት ማድረጋቸው ይታወቃል።