በጌዴኦ ዞን ገቢን በአግባቡ በመሰብሰብ እድገትን ማፋጠን እንደሚገባ ተጠቆመ

65

ዲላ  የካቲት 26/2011 በጌዴኦ ዞን ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ በአግባቡ በመሰብሰብ የዞኑን ሁለንተናዊ እድገት ማረጋገጥ እንደሚገባ ተመለከተ፡፡

የጌዴኦ ዞን የታክስ ንቅናቄ ሳምንት "ግዴታየን እወጣለው መብቴን ጠይቃለው" በሚል መሪ ቃል በስፖርታዊ ውድድሮች ፣ በፓናል ውይይትና በሌሎች መርሀ-ግብሮች እየተከበረ ነው፡፡

በመርሀ ግብሩ ላይ የተገኙት የደቡብ ክልል ገቢዎች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ንጉሴ አስረሰ እንደተናገሩት የጌዴኦ ዞን ቡናን ጨምሮ ከፍተኛ ገቢ ማመንጨት የሚችሉ የኢኮኖሚ አውታሮች አሉ።

ይሁንና ባለፉት ዓመታት መሰብሰብ ያለበት ገቢ በአግባቡ አለመሰብሰቡ ለዞኑ እድገት ተግዳሮት ሆኖ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡

አቶ ንጉሴ እንዳሉት በጌዴኦ ዞን በተያዘው ዓመት ለመሰብሰብ ከታቀደው 495 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢን ማስገኘት የሚችል አቅም መኖሩን በጥናት ተረጋግጧል፡፡

ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ በአግባቡ በመሰብሰብ በዞኑ ሁለንተናዊ እድገትና የህዝብን የልማት ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡

" ግብርን መሰወርና ማጭበርበርን ለመከላከልም ሁላችንም ኃላፊነታችንን ልንወጣ ይገባል" ብለዋል ፡፡

የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ገዙ አሰፋ በበኩላቸው ባለፉት ሁለት ዓመታት በዞኑ ሊሰበሰብ ከታቀደው ገቢ ውስጥ ከ312 ሚሊዮን ብር በላይ ሳይሰበሰብ መቅረቱን ገልፀው ዘንድሮ ይህን ለማስቀረት አተኩሮ መስራት እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡

ግብርን መሰወርና ማጭበርበር ከህዝብ ላይ መስረቅ በመሆኑ ድርጊቱን ለመከላከል ተባብሮ መስራት እንደሚገባ አመለክተዋል፡፡

አቶ ገዙ እንዳሉት የህዝብና የመንግስትን ሀብት በአግባቡ መሰብሰብ ከተቻለ በሌሎች አካባቢዎች ላይ የሚታየውን እድገት ወደ ጌዴኦ ዞን ማምጣትና የህዝቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ይቻላል፡፡

የጌዴኦ ዞን ገቢዎች ባለስልጠን ዋና ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተወልደ ተስፋዬ ባለፉት ሁለት ዓመታት የነበረው ዝቅተኛ የገቢ አፈጻጸም ከተማና ወረዳዎችን በልማት ወደኋላ እንዲቀሩ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡

"በተያዘው በጀት ዓመት በዞኑ 495 ሚሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ብናቅድም እስካሁን ማሳካት የቻልነው 220 ሚሊዮን ብር ብቻ ነው" ብለዋል፡፡

እቅዱን ለማሳካት ከተለመደው አሰራር መውጣትና የገቢ አሰባሰብ ሥርዐቱን ማዘመን እንደሚገባም አቶ ተወልደ ተናግረዋል፡፡

ከኪራይ ሰብሳቢነት የፀዳ አሰራር በመከተል የንግዱ ማህበረሰብም ከሰዶ ማሳደድ አመለካከት መላቀቅና "ግብር የምከፍለው ለሀገሬና ለህዝብ ጥቅም ነው" በሚል እሳቤ የሚጠበቅበትን መወጣት እንዳለበት ገልፀዋል ፡፡

ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱ ግንባር ቀደም ከሆኑ ግብር ከፋዮች ጋር በቅርበት እየሠራ መሆኑን ገልጸው በእዚህም አሁን የተጀመረውን ትብብር አጠናክሮ በማስቀጠል ዞኑን ወደተሻለ ምዕራፍ ለማሸጋገር እነደሚሰራ ጠቁመዋል ፡፡

በዲላ ከተማ በዱቄት ፋብሪካ ሥራ ላይ የተሰማሩት አቶ የሱፍ ጣሃ በበኩላቸው ዞኑ ያለው አቅም ከፍተኛ ቢሆንም ግብር በአግባቡ በመክፈል በኩል ክፍተቶች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡

"በግብር አከፋፈል ላይ ከሌሎች ግንባር ቀደም ግብር ከፋዮችና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየመከርን ነው" ያሉት አቶ የሱፍ፣ በቀጣይ ይብልጥ ተቀራርቦ በመስራት የተያዘውን የገቢ ዕቅድ ለማሳካት ጥረት እንደሚደረግ አመልክተዋል፡፡

ኮንትሮባንድና ሕገ-ወጥ ንግድ ሕጋዊ ነጋዴዎችን እያዳከመ ግብርንም በአግባቡ እንዳይከፍሉ ወደኋላ እያስቀረ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በግብርናና ሆቴል ሥራ ዘርፍ የተሰማሩት አቶ ዳንኤል ሾጦጦ ናቸው።

"ሕገ-ወጥ ንግድን፣ ግብር መሰወርና ማጭበርበርን ለመከላከል የሁሉም ኃላፊነት በመሆኑ የሚጠበቅብንን እንወጣለን" ብለዋል፡፡

በዞን ደረጃ በተካሄደው የፓናል ውይይት ላይ ከሃይማኖትና ከባህል አባቶች እንዲሁም ከንግዱና ከተለያዩ ማህበረሰብ ክፍሎች የተሳተፉ ሲሆን ንቅናቄው በሁሉም ወረደና ከተሞች የሚቀጥል መሆኑ ታውቋል ፡፡ 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም