በሶማሌ ክልል የሰፈነው ሰላም የሕዝብና ቤቶች ቆጠራውን በተሳካ ሁኔታ ለማካሄድ ያስችላል--ኤጀንሲው

74

ጅግጅጋ የካቲት 26/2011 በሶማሌ ክልል የሰፈነው ሰላም የሕዝብና ቤቶች ቆጠራውን በተሳካ ሁኔታ ለማካሄድ እንደሚያስችለው በማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ የጅግጅጋ ቅርንጫፍ ገለጸ።

የቅርንጫፉ ተወካይ አቶ ዮሐንስ ገብረፃዲቅ ለኢዜአ እንዳስረዱት በክልሉ የሰፈነው ሰላም ዘንድሮ በ11ዱም  ዞኖች የሚካሄደውን ቆጠራ ምሉዕ ያደርገዋል ፤ በዚህም አንድም ሰው ሳይታለፍ ለመቁጠር ያስችላል።

ለቆጠራውም ከ7 ሺህ በላይ የቆጠራ ቦታዎች ካርታ እንደተዘጋጀላቸውም ተናግረዋል።

በክልሉ በነበረው አለመረጋጋት ከ12 ዓመታት በፊት በተካሄደው ሦስተኛው የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ በወቅቱ ከነበሩት ዘጠኝ ዞኖች በካርታ የተሸፈኑት ፋፈን፣ ሲቲ፣ ሊበንና አፍዴር ብቻ እንደነበሩ አስታውሰዋል።

በአሁኑ ቆጠራ ግን በሁሉም ዞኖች ቆጠራውን ለማካሄድ ካርታ መዘጋጀቱን አቶ ዮሐንስ አብራርተዋል።

የዘንድሮው ቆጠራ ከሌላው ጊዜ የሚለየው የክልሉ ተወላጆች በቆጣሪነትና በአስቆጣሪነት ሙሉ በሙሉ እንደሚሰማሩበትም ገልጸው ይህም መንገድ መሪ ሳያስፈልጋቸው ሥራውን ለማከናወን ያስችላቸዋል ብለዋል።

እንዲሁም ቆጠራው ከወረቀት ሥራ ወጥቶ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ እንደሚከናወንም አስረድተዋል።

በተቆጣጣሪነት ለሚሰማሩ 377 ባለሙያዎች በዚህ ሳምንት ሥልጠና እንደሚሰጥም ተወካዩ ተናግረዋል።


በቆጠራው የሚሰማሩ ባለሙያዎች ስልጠናና ቁሳቁስ የማጓጓዝ ሥራው እስከ መጋቢት 8/2011 እንደሚጠናቀቅ ገልጸዋል።

በቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ የቴክኒክ ክፍል ኃላፊ አቶ ተገኑ ጌታሁን በበኩላቸው ከ7ሺህ በላይ ቆጣሪዎች በቆጠራው እንደሚሰማሩ አስታውቀዋል።

በዚህም አንድ ቆጣሪ በገጠር 100 እስከ 150 በከተማ 150 እስከ 200 ሰዎች ይመዘግባል ብለዋል።

በኢትዮጵያ አራተኛው የህዝብና ቤት ቆጠራ ከመጋቢት 29 እስከ ሚያዝያ 20/2011 ድረስ ይካሄዳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም