ባጃጅ ታክሲ አገልግሎት ከታሪፍ በላይ መሆን እያማረረን ነው--የነቀምቴ ከተማ ነዋሪዎች

145

ነቀምቴ የካቲት 26 /2011 በነቀምቴ ከተማ በባጃጅ ታክሲ አገልግሎት ከታሪፍ በላይ እየተጠየቁ መቸገራቸውን አንዳንድ የከተማዋ ነዋሪዎች ገለጹ።

በከተማዋ የ09 ቀበሌ ነዋሪ አቶ ንጉሱ ደጀኔ በሰጡት አስተያየት ታክሲዎቹ ሁለት ብር ለሚያስከፍለው መሥመር ሦስት ብር፣ሦስት ብር ለተተመነለት መሥመር ደግሞ አምስት ብር እያስከፈሉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በታክሲዎቹ ላይ  የሚደረገው ቁጥጥርም በመላላቱ ኅብረተሰቡ እየተማረረባቸው ነው ብለዋል፡፡

የ06 ቀበሌ ነዋሪው አቶ ተፈሪ ያደታ በበኩላቸው በከተማው ያለው የታክሲ አገልግሎት ባለቤት የለሽ፣ ሕገወጥነት የተስፋፋበትና ጥቅም ያለአግባብ የሚጠየቅበትአሰራር መንሰራፋቱን ይናገራሉ።

የከተማው የትራንስፖርት ባለሥልጣንና ትራፊክ ፖሊስ የተጣለባቸውን ኃላፊነት በመዘንጋት ቁጥጥርና ክትትል ባለማድረጋቸው ማዘናቸውን ተናግረዋል።

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አቶ ሀብቴ ጥበቡ ታሪፉ በታክሲ ሾፌሮች ፍላጎት ብቻ በመመስረቱ ኅብረተሰቡ ላላስፈላጊ ወጪ እየተዳረገ ነው ብለዋል።

ይህም በከተማው የሕግ የበላይነትን የሚያስከብር አካል አለመኖሩን ያመለክታል ባይ ናቸው።

በከተማዋ ከሚገኙ የባጃጅ አሽከርካሪዎች መካከል ወጣት አማኑኤል ዳዊት ቤንዚን በውድ ዋጋ ገዝቶ ስለሚሰራ የዋጋ ጭማሪ ማድረጉን ገልጿል።

ሌላው አሽከርካሪ ወጣት ገረመው ቀጄላ 110 ብር የነበረው የሞተር ዘይት ዋጋ 165 ብር በመድረሱ  የታሪፍ ጭማሪ ለማድረግ ተገድጄያለሁ ብሏል።

የኦይል ሊቢያ የነቀምቴ ተወካይ ወይዘሪት ሞቱ ኦልጅራ ቤንዚን በታዘዘው መጠንና ጊዜ ስለማይደርስ እጥረት እያጋጠመ መሆኑን አስታውቀዋል።

የነቀምቴ ቶታል ቁጥር ሁለት ተወካይ አቶ ብርሃኑ አጋም በአንድ ጊዜ የሚራገፈው 25 ሺህ ሊትር ቤንዚን አንድ ሳምንት ሳይሸፍን እንደሚያልቅ ተናግረዋል።

የነቀምቴ ከተማ ንግድ ጽህፈት ቤት የንግድ ሥርዓት ተወካይ አቶ መኮንን ከበደ በከተማዋ የሚታየው የቤንዚን እጥረት በታክሲ አገልግሎት ታሪፍ ላይ ጭማሪ የሚያስከትል እንዳልሆነ ገልጸዋል።

የቤንዚን እጥረት እንዳይከሰትም ነዳጅ ማደያዎች ቤንዚን በጀሪካን እንዳይሸጡ መከልከሉንና ቁጥጥርና ክትትል እየተደረገ ነው ብለዋል።

የከተማው የትራንስፖርት ባለሥልጣን ኃላፊ አቶ እንቻለው ሦሩማ በከተማው የአቅርቦት ችግር መኖሩንና ማደያዎች በየሁለት ሳምንቱ  መቅረብ የነበረበት 23 ሺህ ሊትር ቤንዚን እንደማይደርሳቸው አስረድተዋል፡፡

ኅብረተሰቡ ከታሪፍ በላይ ሲጠየቅ ለባለሥልጣኑና ለሚመለከታቸው አካላት እንዲያሳውቅ ያስረዱት ኃላፊው፣የቁጥጥርና ክትትል ሥራውን በማጠናከር ችግሩን ለማቃለል እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡

ነቀምቴ 100 ሺህ ነዋሪዎች እንዳሏት የምትገመት የምሥራቅ ወለጋ  ዞን ርዕሰ ከተማ ስትሆን፣በምዕራብ ኢትዮጵያ ከሚገኙ ታላላቅ ከተሞች አንዷ ናት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም