አንድ መቶ ሺህ የኀብረተሰብ ክፍሎች የሚሳተፉበት ከተማ አቀፍ የቴክኒክና ሙያ ሳምንት መጪው ዕሮብ ይጀምራል

638

አዲስ አበባ የካቲት25/2011 አንድ መቶ ሺህ የኀብረተሰብ ክፍሎች የሚሳተፉበት ከተማ አቀፍ የቴክኒክና ሙያ ሳምንት ከመጪው ዕሮብ አንስቶ በአዲስ አበባ ይካሄዳል። 

”ለኢንዱስትሪ ዕድገታችን ቴክኒክና ሙያ የመጀመሪያ ምርጫችን” በሚል መሪ ሀሳብ ከየካቲት 27 እስከ መጋቢት 1 ቀን 2011 ዓ.ም እንደሚካሄድ ነው የአዲስ አበባ ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ቢሮ ዛሬ በሰጠው መግለጫ ይፋ ያደረገው።    

የቢሮው ኃላፊ አቶ ንጋቱ ዳኛቸው እንደገለጹት፤ ለ9ኛ ጊዜ የሚካሄደው የቴክኒክና ሙያ ሳምንት ዓላማው የቴክንክና ሙያን ስትራቴጂ ተግባራዊ በማድረግ ከየተቋማት ተቀድተው በተሸጋገሩላቸው አዋጭ ቴክኖሎጆዎች እንዲሁም በሚደረግላቸው የኢንዱስትሪ ኤክስቴሽን ድጋፍ ውጤታማ የሆኑ ኢንተርፕራይዞች ምርቶቻቸውን ማስተዋወቅ ነው።     

በቀጣይም ኢንተርፕራይዞች ሊሸጋገሩ የሚችሉ ከ1 ሺህ በላይ ቴክኖሎጂዎችን እንደሚያቀርቡ ገልጸው እነዚህም ግብርና፣ ቆዳና ቆዳ ውጤቶች ብረታ ብረት ከቴክኖሎጂዎቹ ከሚቀርቡባቸው መካከል መሆናቸውን ጠቅሰዋል። 

በዘርፉ በአሰልጣኞችና ሰልጣኞች የተቀዱ ችግር ፈቺ ቴክኖሎጂዎች፣ያሉ ምርጥ ተሞክሮዎችን ለኀብረተሰቡ ማካፈልና የመስኩን አዋጭነት የበለጠ ማጉላት በመርሃ ግብሩ ተካተዋል።    

በመስኩ እየተሰጡ ያሉ አገልግሎቶችን ለባለድርሻ አካላት በማስተዋወቅ በቅንጅት ለመስራት እንዲቻል ሁኔታዎችን ማመቻቸት፣ ስለ ቴክኒክና ሙያ ስትራቴጂ የኀብረተሰቡን ግንዛቤ ማሳደግ፣ በተለያዩ መንገዶች በመስኩ በስራ ዕድል ፈጠራ፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲሁም በሰው ኃይል ልማት የተሰሩ ሥራዎችን ማስተዋወቅም ሌላው የሳምንቱ ዓላማ ነው።  

እንደ አቶ ንጋቱ ገለጻ በቴክኒክና ሙያ ዘርፍ እስካሁን በተከናወኑ ተግባራት በተገኙ ውጤቶችና በቀጣይም መደረግ በሚገባቸው ጉዳዮች ላይ የሚመክርና 300 ተሳታፊዎች የሚገኙበት የፓናል ውይይት የካቲት 28 ቀን 2011 ዓ.ም ይካሄዳል።  

ከቢሮው የተገኘው መረጃ እንደሚጠቁመው በሳምንቱ ከመንግሥት 30 እንዲሁም ከግል 80 ቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት የሚሳተፉበት ሲሆን ከ600 በላይ ሞዴል ኢንተርፕራይዞች በመርሃ ግብሩ ላይ ይሳተፋሉ።   

የአዲስ አበባ ከተማ ከፍተኛ የመንግስት አመራሮች፣ የህዝብ ተወካዮች፣  የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ዳይሬክተሮች፣ የወላጅ ተማሪ ህብረት አመራሮችና የቴክኒክና ሙያ አሰልጣኞች የሚሳተፉ ሲሆን በአጠቃላይ 100 ሺህ የኀብረተሰብ ክፍል እንደሚሳተፍ ነው የታቀደው።