ለአርሶ አደሩ የሚቀርበው የግብርና ግብአት አሰራር መሻሻሉ ብድር በወቅቱ እንዲመለስ እያደረገ ነው

93

ደብረ ማርቆስ 24/6/2011 በምስራቅ ጎጃም ዞን ለአርሶ አደሩ የሚቀርበው የግብርና ግብአት በኩፖን አሰራር እንዲሆን መደረጉ ብድር በወቅቱ እንዲመለስ ማስቻሉን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።

የመምሪያው የግባት አቅርቦትና ስርጭት የሥራ ሂደት ቡድን መሪ አቶ ኃይለኢየሱስ ዳምጤ ለኢዜአ እንደተናገሩት የኩፖን ስርዓቱ በብድር ለአርሶ አደሩ የሚሰጠውን የግብዓት ገንዘብ በወቅቱ እንዲመለስ እያገዘ ነው፡፡

ከአማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም ጋር በመተባበር የግብርና ግብአት እጅ በእጅ ሽያጭ መግዛት የማይችሉ አርሶ አደሮች ከተቋሙ ብድር በመውሰድ ገንዘቡን በወቅቱ እንዲመልሱ ማድረግ ያስቻለ አሰራር መሆኑንም አስረድተዋል።

ቡድን መሪው እንዳሉት ከዚህ በፊት የግብአት ስርጭቱ በማህበራት በኩል በነበረበት ወቅት እስከ 3 ዓመት የሚቆይ ብድር ለአርሶ አደሩ ቢሰጥም ገንዘቡን  ለማስመለስም ችግር ነበር፡፡

ቀደም ሲል በነበረው አሰራር ቢበዛ በየዓመቱ 50 በመቶ ያህል ብቻ ብድር እንደሚመለስ ያስታወሱት አቶ ኃይለኢየሱስ የኩፖን አሰራር ተግባራዊ ከሆነ ወዲህ በየዓመቱ ብድሩን ሙሉ በሙሉ ለማስመለስ መቻሉን አብራርተዋል፡፡

ባለፈው ዓመት ብቻ ለምኽር እርሻ በብድር ከተሰራጨው ከ311ሚሊዮን ብር ውስጥ እስካሁን ከ260 ሚሊዮን በር በላይ መመለሱን በማሳያነት ጠቅሰዋል፡፡

ቀሪው ገንዘብ የዘንድሮ የግባት ስርጭት እስኪጀመር ድረስ ሙሉ በሙሉ ተመላሽሆናል ብለዋል፡፡

ከተጠቃሚዎች መካከልም የአነደድ ወረዳ የጉድ አለማ ቀበሌ ነዋሪ አርሶአደር ዘርያለው አወቀ በበኩላቸው ቀደም ሲል በሕብረት ሥራ ግብአት ለማግኘት ማህበራት በኩል የነበረው አሰራር ግልፅነት የጎደለው እንደነበር ገልጸዋል፡፡

በዚህም የፈለጉትን ኩንታል ማዳበሪያ መውሰድ እንደማይቻል አስታውሰው አሁን ላይ ቀድሞ በሚካሄድ የብድር ግብይት ያለምንም ችግር የፈለጉትን ያህል ማዳበሪያ እያገኙ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በመኽር እርሻ ወቅት ማዳበሪያ በብድር በመውሰድ  ምርቱን ሰብስበው ከሸጡ በኋላ ብድራቸውን የሚመልሱ መሆኑ ለስራቸው ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸውም አብራርተዋል፡፡

የማቻከል ወረዳ የየውላ ቀበሌ ነዋሪ አርሶአደር አብነት መኩሪያው በበኩላቸው "የግብአት ግብይቱ በአብቁተ በኩል መሆኑ በፊት ይፈጸምብኝ የነበረውን አድሎአዊ አሰራር አስቀርቶልኛል" ብለዋል።

"ከዚህ በፊት ካለብኝ የገንዘብ እጥረት ግባአት በብድር እንዲሰጠኝ ስጠይቅ 'ከቀበሌ አስመስክር' እየተባለ ስለሚጓተት ግብአት ያልቅ ነበር፤ የሚሰጠኝም ከምፈልገው በታች ነበር"ሲሉም ገልጸዋል።

"አሁን ግን ብድሩን እከፍላሉሁ ብዬ ከአብቁተ እስከተበደርኩ ድረስ የሚያስፈልገኝን ያህል ግብአት ወስጄ መጠቀም እየቻልኩ ነው፤ ብድሬንም በወቅቱ እየመለስኩ ነው" ብለዋል።

ባለፈው ዓመት በኩበፐን በተካሄደው የግብይት አሰራር 128 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች ተጠቃሚ መሆናቸውንና እስካሁንም አብዛኛው ብድራቸውን መመለስ እንደቻሉ ታውቋል፡፡

በዞኑ ለቀጣዩ የመኽር ወቅት ጥቅም ላይ የሚውል ከ1 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ለማስገባት ታስቦ እስካሁን 240 ሺህ ኩንታል ማስገባት ተችሏ ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም