በስሑል ሽሬ ሆስፒታል በተደረገልን የዓይን ቀዶ ሕክምና ማየት ችለናል--- ተጠቃሚዎች

77

ሽሬ የካቲት 24/2011 በስሑል ሽሬ ሆስፒታል በተደረገላቸው ነጻ የዓይን ቀዶ ሕክምና ማየት እንደቻሉ የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ገለጹ።

የአክሱም ዩኒቨርሲቲ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል "ሂማልያ ካትራክት ፕሮጀክት" ከተባለ የአሜሪካ ግብረ ሰናይ ድርጅት ጋር በመተባበር  ለ700 ሰዎች ነጻ የዓይን ቀዶ ሕክምና መስጠቱን አስታውቋል።

አገልገሎቱን ካገኙ መካከል የ70 እና 75 ዓመት የዕድሜ ባለፀጎች አቶ በሪሁ ኢብራሂምና ወይዘሮ ለተኪዳን ወርቀልኡል ይገኙበታል።

የተደረገላቸው የዓይን ሞራ ቀዶ ሕክምና ለዓመታት ማየት ተስኗቸው የቆዩ አይኖቻቸው ብርሃናቸው እንዲመለስ ማድረጉን ተጠቃሚዎቹ ተናግረዋል።

አቶ በሪሁ ኢብራሂም  “በሰው እርዳታ መጥቼ ከህክመናው በኋላ ራሴን ችዬ መራመድ መቻሌ ዳግም እንደተፈጠርኩ ያክል እንዳስብ አስችሎኛል” ብለዋል።

“ቀደም ሲል ወደ ቤተክርስቲያንም ሆነ በቤቴ ውስጥ ለመንቀሳቅስ ሰው አስችግር ነበር፤ ሕክምናው ከተደረገልኝ ወዲህ ግን ራሴን ችዬ መንቀሳቀስ በመቻሌ እድለኛ ነኝ” ያሉት ደግሞ ወይዘሮ ለተኪዳን ወርቀልኡል ናቸው።

ወጣት በላይ አሰፋ በበኩሉ በትራኮማ ምክንያት ለአንድ ዓመት ያህል ብርሃኑን አጥቶ መቆየቱን አስታውሶ በተደረገለት ነጻ ሕክምና የዓይኑ ብርሀን ተመልሶ ያለችግር ሥራውን ማከናወን እንደቻለ ተናግሯዋል።

የነጻ የዓይን ሕክምናው ቡድን መሪና የዓይን ሕክምና ስፔሻሊስት ዶክተር ተስፋአለም ሐጎስ በበኩላቸው የሕክምና አገልግሎቱ ከየካቲት 18 እስከ 24 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ መሰጠቱን ተናግረዋል።

"ለሰባት ቀን በተሰጠው ሕክምናም ለ560 ወገኖች የዓይን ሞራ ማስወገድ ሕክምና እንዲሁም ለ140 ሰዎች በትራኮማ ሳቢያ የሚመጣን የዓይን በሽታ የመከላከል ሥራ ተከናውኗል" ብለዋል።

ከግብረ ሰናይ ድርጅቱ ጋር በመሆን በተጀመረው የሕክምና አገልግሎት ለቀጣይ አምስት ዓመት ከ60 ሺህ በላይ ሰዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ግብ መያዙንም አመላክተዋል።

የሽሬ እንዳስላሴ ስሑል ዞናል ሆስፒታል የዓይን ሕክምና ክፍል አስተባባሪ አቶ ፀጋይ ሐጎስ የነጻ ሕከምናው አቅመ ደካሞችን ተጠቃሚ ማድረጉን ገልጸዋል።

በተለይ ታክመው መዳን እየቻሉ በገንዘብ እጦት ለዓመታት ብርሃናቸውን አጥተው ቤታቸው ለተቀመጡ የሕብረተሰብ ክፍሎች ሕክምናው መሰጠቱን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም