በክልሉ በለሙ ተፋሰሶች አርሶ አደሩ በባለቤትነት እንዲጠቀም እየተደረገ ነው

58

ባህር ዳር የካቲት 24/2011 በአማራ ክልል ከእንስሳት ልቅ ግጦሽ ነጻ የሆኑ 4 ሺህ 659 የለሙ ተፋሰሶችን ለአርሶ አደሩ በባለቤትነት በማስረከብ በዘላቂነት እንዲጠበቁ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ ገለፀ።

የቢሮው የተፈጥሮ ሃብት ልማት ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው እንግዳየሁ ለኢዜአ እንዳሉት ባለፉት ሰባት ዓመታት የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ የተከናወነባቸው 18 ሺህ ተፋሰሶች ወደ ልማት ገብተዋል።

በእነዚህ ተፋሰሶች አርሶ አደሩን በማሳተፍ የእርከን፣ የክትር፣ የእርጥበት ማቆያ ስትራክቸሮች፣ ከእንስሳት ንክኪ የመጠበቅና በችግኝ ተከላ የማጠናከር ሥራ ተሰርቷል፡፡

የለሙ ተፋሰሶችን ከእንስሳት ልቅ ግጦሽ ሙሉ በሙሉ መከላከል የተቻለ ሲሆን በተደረገው ጥበቃና እንክብካቤ ቀድመው ማገገም የቻሉትን በመለየት አርሶ አደሩ በባለቤትነት ተረክቦ እንዲያስተዳድራቸው መደረጉን ተናግረዋል።

በተላለፉ ተፋሰሶች ከ300 ሺህ የሚበልጡ አርሶ አደሮች በግልና በቡድን ሆነው በንብ ማነብና በእንስሳት እርባታ፣ በእንስሳት ማድለብ፣ በፍራፍሬና በደን ልማት ሥራ በመሰማራት ተጠቃሚ መሆናቸውን አቶ ጌታቸው ገልጸዋል።

በቀጣይም ወደተጠቃሚነት ያልተሸጋገሩ ተፋሰሶችን በአግባቡ አልምቶ ለአርሶ አደሩ በባለቤትነት ለማስተላለፍና በዘላቂነት እንዲጠበቁ ለማድረግ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።        

በዘንድሮ የበጋ ወራትም ከምዕራብ ጎንደር ዞን በስተቀር በሌሎች የክልሉ ዞኖችና ወረዳዎች የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራ ከጥር 2 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ በመከናወን ላይ መሆኑንም አቶ ጌታቸው አስታውቀዋል፡፡

አቶ ጌታቸው እንዳሉት ከወቅታዊ ሁኔታ ጋር በተያያዘ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራው በአሁኑ ወቅት ተቀዛቅዟል።

ለእዚህም በበጋ ወራት ለመስራት ከታቀደው 478 ሺህ ሄክታር መሬት ውስጥ እስካሁን ማከናወን የተቻለው ከ22 ነጥብ 5 በመቶ ብቻ መሆኑን በማሳያነት ጠቅሰዋል፡፡

በደቡብ ጎንደር ዞን ፋርጣ ወረዳ የአውዘት ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ባህሩ ድረስ በበኩላቸው የአለቅት ወንዝ ተፋሰስን በባለቤትነት ተረክበው በመጠበቅና በማልማት ተጠቃሚ መሆን መጀመራቸውን ገልጸዋል፡፡

ልቅ ግጦሽን በማስቆም ከተፋሰሱ በሚያገኙት በቂ መኖ እንስሳትን አስረው በመቀለብ የተሻለ ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራው የለሙ አካባቢዎች የከርሰ ምድር ውሃ በመቆፈር በጓሯቸው ተጨማሪ ገቢ የሚያስገኙ የጓሮ አትክልቶችን ለማልማት እንዳስቻላቸውም ተናግረዋል።

በምዕራብ ጎጃም ዞን ሰሜን ሜጫ ወረዳ የእናምርት ቀበሌ ነዋሪ ወጣት ደህንነት አደመ በበኩሉ ወደተጠቃሚዎች በተላለፈው ተፋሰስ 10 ሆነው በመደራጀት በከብት እርባታ ሥራ እንደተሰማሩ ተናግሯል።

አሁን ካሏቸው አምስት የተሻሻሉ የወተት ላሞች በቀን የሚያገኙትን ከ45 እስከ 65 ሊትር ወተትለተረካቢዎችበመሸጥ እስከ 600 ብር ገቢ እያገኙ መሆናቸውን አስረድተዋል።

የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራ የህልውና ጉዳይ መሆኑን በመረዳትም የዘንድሮውን የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ያለማንም አነሳሽነት በራሳቸው እያከናወኑ መሆናቸውንም አርሶ አደሮቹ አስረድተዋል። 

በክልሉ ባለፉት ሰባት ዓመታት በህዝብ ንቅናቄ በ6 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ መከናወኑም ታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም