በመኽሩ ከ4 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት ለማልማት ዝግጅት እየተደረገ ነው

60

ባህር ዳር  የካቲት 24/2011 በአማራ ክልል በመጪው የመኽር ወቅት የተሻሻሉ የግብርና አሰራሮችን በመጠቀም ከ4 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት ለማልማት የእርሻ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ ዶክተር ሰሎሞን አሰፋ ለኢዜአ እንደገለጹት በ2011/2012 የመኽር እርሻ የተሻሻሉ የግብርና የአሰራር ዘዴዎችን በመጠቀም ከሚለማው መሬት 120 ሚሊዮን ኩንታል ይሰበሰባል።

ዝናብ መጣል እንደጀመረ የዘር ሥራውን ለማከናወን ከወዲሁ የተጠናከረ የእርሻ ሥራ በአርሶ አደሩ እየተከናወኑ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በዘር ከሚሸፈነው መሬት ውስጥ 3 ሚሊዮን ሄክታሩ በኩታ ገጠም እርሻ የሚለማ ሲሆን፣ "ይህን ለማሳካትም በመጋቢት ወር ለግብርና ባለሙያዎችና አርሶአደሮች ስልጠና መስጠት ይጀመራል" ብለዋል፡፡

ስልጠናው በኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴ፣ በእርሻና በምርት ማሳደጊያ ግብዓት አጠቃቀም፣ በአረም አወጋገድ፣ በተባይ ፍተሻና በሌሎች የተሻሻሉ የግብርና አሰራሮች ላይ የሚያተኩር ነው።

ዶክተር ሰለሞን እንዳሉት ለመጪው የመኽር እርሻ የሚውል 5 ነጥብ 3 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ግዥ ተፈጽሞ ከውጭ ወደሀገር ውስጥ በመጓጓዘ ላይ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ከዚህ ውስጥ እስካሁን ከ200 ሺህ ኩንታል በላይ የሚሆነው ማዳበሪያ ከወደብ ወደክልሉ ተጓጉዞ መድረሱንም አስረድተዋል።    

በምዕራብ ጎጃም ዞን ወንበርማ ወረዳ የሽንዲ ቀበሌ የሰብል ልማት ጥበቃ ባለሙያ አቶ ባንተጊዜ ጌታሁን በበኩላቸው አርሶ አደሩ ያለፈውን ሰብል በመሰብሰቡ መሬቱን ከወዲሁ እያረሰ እንደሚገኝ ተናግረዋል። 

የተጀመረውን ኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴ ከማጠናከር ባለፈ በቂ ማዳበሪያና የምርጥ ዘር ግብዓት ተጠቅሞ አርሶአደሩ እንዲያለማ በቅርበት ሆነው ሙያዊ ድጋፍ እያደረጉ መሆናቸውን አስረድተዋል።

በእዚሁ ወረዳ የዋዝንክስ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አምሳሉ ቆለጭ ኩታገጠም የአስተራረስ ዘዴን ተግባራዊ ካደረጉ ካለፉት ሦስት ዓመት ጀምሮ የበቆሎ ምርትን በሄክታር ከ35 ወደ 50 ኩንታል ማሳደጋቸውን ተናግረዋል።

በቀጣዩ የመኽር ወቅትም የተሻሻሉ አሰራሮችንና በቂ የምርት ማሳደጊያ ግብዓትን ተጠቅመው በማልማት የሚያገኙትን ምርት ለማሳደግ ከወዲሁ የእርሻ ስራ መጀመራቸውን ገልጸዋል።

ኩታገጠም የአስተራረስ ዘዴን ተጠቅመው ማልማታቸው በሄክታር ያገኙት የነበረን 40 ኩንታል የበቆሎ ምርት ወደ75 ኩንታል በማሳደግ ተጠቃሚ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ በምዕራብ ጎጃም ዞን ደንበጫ ወረዳ የእግዚአብሔር አብ ቀበሌ አርሶ አደር አብራራው ፈንቴ ናቸው።

በመጭው መኽርም ከአለኝ አራት ሄክታር መሬት ሦስቱን በኩታገጠም በበቆሎ ሰብል በመሸፈንና በቂ ማዳበሪያ በመጠቀም እስከ 250 ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ አቅደው እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ኩታገጠም የአስተራር ዘዴ የባለሙያን ምክር በአንድ ቦታ ለማግኘት፣ የምርት ማሳደጊያ ግብዓት በአግብቡ ለመጠቀምና ሌሎች ተግባራትን በማከናወን የተሻለ ምርት እንዲያገኙ ያደረጋቸው መሆኑን አርሶ አደሮቹ አስረድተዋል።      

በክልሉ በ2009/2010 የምርት ዘመን ከለማው መሬት 100 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል ምርት መገኘቱ ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም