ችግር ፈቺ አዳዲስ ፈጠራዎችን መስራታቸን የፈጠራ ስራ ውድድር አሸናፊ አድርጎናል-ተማሪዎች

184
ሀዋሳ ግንቦት 22/2010 የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ባደረገላቸው ድጋፍ ችግር ፈቺ የሆኑ አዳዲስ ፈጠራዎች  መስራት እንደቻሉ የፈጠራ ስራ ውድድር አሸናፊ ተማሪዎች ተናገሩ፡፡ ከአሜሪካ ኤምባሲ ጋር በመተባበር በደቡብ ህዝቦች ክልል ደረጃ በተካሄደው የፈጠራ ስራ ውድድር ላይ ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ደረጃ በመውጣት አሸናፊ ለሆኑ ተማሪዎች ትናንት እውቅና ተሰጥቷል፡፡ በዚህ ወቅት አሸናፊ ተማሪዎች  ለኢዜአ እንዳሉት የፈጠራ ሀሳባቸውን ወደ ተግባር  መለወጥ ችለዋል፤ ለዚህ ውጣት አንዲበቁም  ዩኒቨርስቲ ከትምህርታቸው በተጓዳኝ ስራ ፈጣሪ ሆነው እንዲወጡ ባቋቋመው ኢንኩቤሽን ማዕከል ድጋፍ አርጎላቸዋል፡፡ በዩኒቨርስቲው የኤሌክትሮ ሜካኒካል ምህንድስና የሶስተኛ ዓመት ተማሪው ሄኖክ አዲሱ በሰጡው አስተያየት የአፈሩን እርጥበት መጠንና የአየር ሁኔታውን በመለካት ያለ ሰው ንክኪ በራሱ ውሃ ማጠጣት የሚያስችል አዲስ የመስኖ ውሀ ማጠጫ ፈጠራ ባለቤት መሆን እንደቻለ ተናግሯል፡፡ ፈጠራው ለትላልቅና አነስተኛ የመስኖ ልማት ስራ ጥቅም ላይ መዋል እንደሚችልና የውሀ ብክነት ማስቀረት እንደሚያስችል ጠቅሶ ገልጾ  ለውድድር ይዞ በቀረበው የፈጠራ ስራም አንደኛ በመውጣት ወደ ቀጣዩ ሀገር አቀፍ ውድድር ማለፉን ገልጿል፡፡ በዩኒቨርሲቲው የጤና ሳይንስ ኮሌጅ የህክምና የስድስተኛ ዓመት ተማሪው ሚፍታ ሰይድ በበኩሉ ህብረተሰቡ በሽታን አስቀድሞ ለመከላከልና የጤና እንክን ሲጋጥመውም ህመሙን ለይቶ  አቅሙን ባገነዘበ ክፍያ በመረጠው  የጤና ተቋም እንዲታከም በቀላሉ በሞባይል ስልክ መረጃ ማግኘት  የሚስችል አፕሊኬሽን  ከጓደኛው ጋር መስራታቸውን ተናግሯል፡፡ በዚህም ተወዳድረው  በጋራ ሁለተኛ ደረጃን ማግኘታቸውን ጠቅሷል፡፡ በሰራው አዲስ ፈጠራ የሶስተኛ ደረጀን ያገኘው ደግሞ በሀዋሳ አዲስ ከተማ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ11ኛ ክፍል የመሰናዶ ተማሪ  ሲሳይ ሶርሳ ነው፡፡ ደረጃውን ያገኘው ለባለሀብቶች እንዲሁም አዲስ የፈጠራ ሀሳብ ይዘው በገንዘብ እጥረት ወደ ተግባር ያልገቡ ምሩቃን በገበያ አማራጮች ዙሪያ መረጃ የሚሰጥ ሶፍት ዌር በመስራቱ እንደሆነ ተማሪ ሲሳይ ተናግሯል፡፡ በዩኒቨርሲቲው የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ዳይሬክተር ዶክተር ተስፋዬ ባዩ እንዳሉት ተማሪዎች በስራ ፈጠራ አዲስ እውቀት እንዲቀስሙ ለሙከራ ስራቸው ድጋፍ እየተደረገላቸው ነው፡፡ አዲስ የፈጠራ ስራ ያላቸውን ተማሪዎች በስልጠና በማገዘ ሃሳባቸውን አጎልብተው በሙከራ እንዲያረጋግጡ በዩኒቨርሲቲው ኢንኩቤሽን ማዕከል በመስኩ የሰለጠነ መምህር በመመደብ ወደ ተግባር እንዲለውጡ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በአሜሪካ ኤምባሲ አይኮግስ ላብ የተባለው ፕሮጀክት ማኔጀር ወይዘሪት ቤተልሔም ደሴ በኩሏ ተማሪዎች ያላቸውን አዲስ የፈጠራ ሀሳብ በማውጣት የማህበረሰቡን ችግር መፍታት እንዲችሉ ለማድረግ በዘጠኝ ክልሉች የፈጠራ ስራዎች ውድድር እያካሄዱ መሆናቸውን ተናግራለች፡፡ በሀገሪቱ ከሚገኙ 26 ዩኒቨርሲቲዎች ከሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እንዲሁም ከመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ  ሚንስቴር ጋር በመተበባበር እየተሰራ እንደሚገኝም አመልክተዋል፡፡ በደቡብ ህዝቦች ክልል ደረጃ በተካሄደው  ውድድር  ከተሳተፉት መካከል በአሸናፊነት የተለዩት ሶስት ተወዳዳሪዎች በሀገር አቀፍ ደረጃ አዲስ አበባ ለሚደረገው የመጨረሻ ፉክክር ማለፋቸውን ጠቅሰዋል፡፡ ተወዳዳሪዎቹ የፈጠራ ስራዎቻቸውን ይዘው በፉክክሩ እንዲሳተፉ የሰባት ሳምንት ስልጠና እንደተሰጣቸውም ተመልክቷል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም