አውደ ርዕዩ ልምድ ለመለዋወጥና ሥራችንን ለማስተዋወቅ ረድቶናል..ተሳታፊ ተማሪዎች

82
ሐረር ግንቦት 22/2010  የሳይንስና ሒሳብ ትምህርት ፈጠራ ውጤቶች አውደ ርዕይ ተሞክሮ ለመቅሰምና ለትምህርቶቹ የተለየ ትኩረት ለመስጠት እንዳነሳሳቸው በሐረር ከተማ በተዘጋጀ አውደ ርዕይ ላይ የተሳተፉ ተማሪዎች ገለጹ። በክልሉ ለአምስተኛው ጊዜ የተዘጋጀው የተማሪዎች የሳይንስና ሒሳብ ትምህርት የፈጠራ ሥራ አውደ ርዕይ ትናንት ተጠናቋል። በሐረር ከተማ መንፈሳዊ የመጀመረያ ደረጃ ትምህርት ቤት የ8ኛ ክፍል ተማሪ አማን ካሳሁን  በክልሉ በየዓመቱ የሚዘጋጀው የሳይንስና ሒሳብ የፈጠራ ውጤቶች አውደ ርዕይ እርስ በርስ ልምድ ለመለዋዋጥ እያገዘን ነው ብላለች። "በአውደ ርዕዩ በተማሪዎች ተሰርተው ሚቀርቡ የፈጠራ ውጤቶችን በመመልከት ከምናገኘው ተሞክሮ ባለፈ የፈጠራ ክህሎታችን እንዲነሳሳ አድርጎናል" ብላለች። የጀግኖች የመጀመርያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ሐና አምሳሉ በበኩሏ " አውደ ርዕዩ በየዓመቱ መዘጋጀቱ በራስ የመተማመን ብቃታችን እንዲጨምር ከማድረግ ባለፈ ያለንን የፈጠራ ተሰጥኦ ለሌሎች ለማስተዋወቅ ዕድል ፈጥሮልናል" ብላለች። የአውደ ርዕዩ መዘጋጀት ተማሪዎች በየጊዜው በፈጠራ ሥራዎች ላይ የመሳተፍ ዝንባሌያቸው እንዲጨምር ማድረጉን የገለጹት ደግሞ የአቦከር አንደኛ ደረጃ የፊዚክስ መምህር መብራቱ ገብረ መስቀል ናቸው። በመምህራኑም ዘንድ መነቃቃት እየፈጠረ መሆኑን የገለጹት መምህር መብራቱ፣ ይህም መምህራን ተማሪዎቻቸው የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ ጠንክረው እንዲሰሩ የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል። በአውደ ርዕዩ ላይ የተሳተፉ ተማሪዎችና መምህራኑ እንዳሉት በየትምህርት ቤታቸው በሚገኙ ቤተ ሙከራዎች ለፈጠራ ሥራቸው የሚያገለግሉ የቁሳቁስና የኬሚካል እጥረትን ችግር የሐረሪ ክልል ትምህርት ቢሮ እንዲቀርፍላቸው ጠይቀዋል። በትምህርት ቢሮው የሳይንስ ስርዓተ ትምህርት ተጠሪና የአውደ ርዕዩ አስተባባሪ አቶ ከማል አብዱልባሲጥ በበኩላቸው የሳይንስና ሒሳብ ፈጠራ ውጤቶች አውደ ርዕይ ላለፉት አምስት ዓመታት መዘጋጀቱን ገልጸዋል። ይህም በተለይ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች በሒሳብና ሳይንስ ትምህርቶች ላይ ያላቸው ፍላጎትና ክህሎት እየዳበረ እንዲመጣ የራሱን አስተዋጽኦ ማድረጉን አስረድተዋል። በየዓመቱ በሚዘጋጁ አውደ ርዕዮች አዳዲስ የፈጠራ ሥራዎች በተማሪዎች እየቀረቡ መሆናቸውን የገለጹት አቶ ከማል፣ ከቤተ ሙከራና ተያይዘው የሚነሱ የትምህርት ግብአቶች እጥረትን ለመፍታት ትምህርት ቢሮው ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል። አስካሁንም ከየትምህርት ቤቶች ተጨባጭ ሁኔታ ያለውን ችግር በጥናት የመለየት ሥራ መሰራቱንና በቀጣይ የሚያስፈልገውን ኬሚካልም ሆነ የቤተሙከራ መሳሪያዎችን የማሟላት ሥራ እንደሚሰራ አስረድተዋል። በሐረር ከተማ ለሁለት ቀን በተዘጋጀ የሳይንስና ሒሳብ የፈጠራ ውጤቶች አውደ ርዕይ 29 የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የተሳተፉ ሲሆን ከ200 በላይ የፈጠራ ሥራዎችም ለዕይታ መቅረባቸው ታውቋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም