አድዋ ድል በዓል በመስቀል አደባባይ ተከበረ

83

አዲስ አበባ የካቲት 23/2011የአድዋ ድል በዓል ዛሬ በአዲስ አበባ መስቀል አደባባኝ በደማቅ ሁኔታ ተከብሯል።

ከአዲስ አበባ ዙሪያ ወደ አደባባዩ የመጡ ፈረሰኞች ለበዓሉ ልዩ ድምቀት ሰጥተውታል።

በተለያዩ አርቲስቶች የቀረበው የሙዚቃው ዝግጅትም የሰላምንና የአንድነትን አስፈላጊነት የሚያጎላ ነበር። 

የዛሬ 123 ዓመት ጀግኖች ኢትዮጵያውያን የጣሊያንን ወራሪ ጦር ድል ነስተው ለአፍሪካ የነጻነት ጮራ የፈነጠቁበት እለት መሆኑን ለማስታወስ በተዘጋጀው ፌስቲቫል ላይ ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ ነዋሪዎች ታድመውበታል። 

የአድዋ ድል የኢትዮጵያውያን ኩራት፣ የክብር ማኅተም፤ የጥቁር ህዝቦች የነፃነት ተጋድሎ ቀንዲል ስለመሆኑ ብዙዎች የመሰከሩት ነው።

በጦርነቱ ወቅት በባዶ እግራቸው የተጓዙ ኢትዮጵያዊያን አባት አርቦኞች ገድልን ለመዘከር የአርበኞችን ልብስ ለብሰው በዓሉን እያከበሩ ያገኘናቸው ወጣቶች አባቶች የከፈሉትን መስዋዕትነት ወጣቱ "የአገሪቷን አንድነት በማጠናከር ሊያስቀጥል" ይገባል ብለዋል።

'አባቶቻችን ጠላትን ድል የነሱት በአንድነት ለአንድነት ለመዋደቅ ቆርጠው ስለዘመቱና ስለተዋጉ ነው' የሚል ሀሳባቸውንም ነው የሰጡት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሪፖርተር በመስቀል አደባባይ በተካሄደው የሙዚቃ ድግስ ላይ ወጣቶቹን አነጋግሯል።

የአድዋ ድል አባቶቻችን በአንድነት ጠላት ወራሪን ለማሸነፈ መስዋዕትነት የከፈሉበት መሆኑን ያመለከቱት ወጣቶቹ፤ ጀግኖች አባቶች ያስረከቡትን የአገር አንድነት ማስቀጠል እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።

ወጣት የህይስ ቀለመወርቅ "እኛ የኢትዮጵያ ልጆች ነን።አንድነታችን ነው ዘላላማዊ ሊያደርገን የሚችለው።ደማችን አንድ ሆኖ ተሳስረን። እንተ በእኔ እኔ በአንተ ታስሬ ነው እንጂ ልዩነት  ፈጥረን ማናችንም ወድቀን እንቀራለን እንጂ ልዩነት አንፈጥርም። በዚህ ስሜት ውስጥ መኖር የሚችል ኢትዮጵያዊ ካለ ሁሉም አንድ ነው።ይሄን ስሜት ማምጣት የምንችለው ኢትዮጵያዊ ስሜት ሲኖረን እንጂ ተበታትነን ማንም ለማንም አይኖርም መውደቅ ነው።"ብሏል፡፡

ወጣት ዮሐንስ ገብረስላሴ በበኩሉ "እንደ አንድነታችን ሁላችንም ሰሜን ምዕራብ ደቡብ ምስራቅ ሳንል ሁላችም በህብረት ድሮ እነሱ አንድ ሆነው አገራችንን ለማስከበር ነው የሄዱት አሁን እኛ ዘር ፖለቲካ ሳንል ሁላችንም በአንድነት አንድ ላይ ሆነን ለማክበር ያበቃን አምላክ ይመስገን፤ ከዚህ በበለጠ ሁላችንም የበዓሉን ታሪክ እያወቅን፤ ከዚህ ቀደም ታሪኩን እንድናውቅ የሚያደርግ ነገር አልነበረም አሁን ከዚህ በኋላ ያለው ለውጥ ራሱ ለእኛ ትልቅ መነቃቃት ነው።" ሲል ጠቁሟል፡፡

ወጣት አህመድ ኑር መሃመድ በበኩሉ ከእነሱ በላይ ጠንክረን አገራችንን መጠበቅ አለብን፤ከአባቶቻችን በላይ አገራችንን ጠብቀን ወደ ፊት እናስረክባለን በማለት አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡

የአድዋ ድል ለመጀመሪያ ጊዜ የተከበረው በሠባተኛ ዓመቱ በ1895 ዓ.ም (እ.ኤ.አ በ1903) ከአንድ መቶ ሀያ ሶስት ዓመት በፊት አሁን ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ያለበት ሥፍራ ምኒሊክ አደባባይ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም