በመቱ ከተማ የሚካሄዱ ግንባታዎች በህብረተሰቡ ላይ ጉዳት እንዳያስከትሉ ቁጥጥሩ እንደሚጠናከር ተገለጸ

76

መቱ የካቲት 23/2011 በመቱ ከተማ ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚካሄዱ ግንባታዎች ህጋዊ መንገድ እንዲከተሉና በህብረተሰቡ ላይ ጉዳት እንዳያስከትሉ የክትትልና ቁጥጥር ስራ እንደሚያጠናክሩ የከተማው አስተዳደር ከንቲባ ገለጹ፡፡

በከተማው  ሰሞኑን የግንብ አጥር ተደርምሶ የአንድ ቤተሰብ አባል የሆኑ የሰባት ሰዎች ህይወት ማለፉ ይታወሳል፡፡

ይህንን ተከትሎ የኢዜአ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የመቱ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ  ቀልቤሳ ቶሌራ  እንዳሉት ከዚህ ቀደም  ለተለያዩ አገልግሎቶች ተብሎ በከተማው ሲካሄዱ በቆዩ ግንባታዎች ላይ  ተገቢውን ክትትልና ቁጥጥር  አልነበረም፡፡

ለቆሻሻ ማስወገጃ፣ ለአጥርና ለመሳሰሉት አገልግሎት  ህብረተሰቡ ከሚያካሄዳቸው ግንባታዎች አንዳንዶቹ በቸልተኝነት፣ በተገቢው መሳሪያና ቦታ  ተፈጸሚ ስለማይሆኑ ጉዳት እያስከተሉ ነው፡፡

ለዚህም ማሳያው በከተማው  ሰሞኑን የግንብ አጥር ተደርምሶ የደረሰውን አደጋ ጠቅሰዋል፡፡

ከለውጡ ወዲህ በከተማው አዲስ አመራር ወደ ኃላፊነት በመምጣቱ በህገወጥ ግንባታና በጥራት መጓደል የሚከሰቱ  ችግሮችን ከህብረተሰቡ ጋር በመሆን ተግባራዊ እርምጃ መውሰድ መጀመሩንም አመልክተዋል፡፡

ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት አስተዳደሩ የተጠናከረ ክትትልና  ቁጥጥር እንደሚያደርግ አስታውቀዋል፡፡

ሰሞኑን ለደረሰው አደጋ መንስኤ የሆነው የአጥር ባለቤት በህግ ቁጥጥር ስር ውሎ የማጣራት ስራ እየተካሄደ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

ከንቲባው እንዳሉት ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው የቀበሌ አመራር አካላት እና ባለሙያዎች ላይም  ምርመራ እየተካሄደ ነው፡፡

የመቱ ወረዳ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት አቶ አዲሱ አብዲሳ በበኩላቸው ለሰዎች ሞትና ግጭት ምክንያት ከሆኑ ነገሮች ዋነኛው የሌላውን ደህንነት ከግንዛቤ ባለማስገባት በአንድ ወገን ጥቅም ብቻ  የሚከናወኑ  ተግባራት መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ህብረተሰቡ ለግል ጥቅም በማሰብ በወሰን ላይ የሚተክላቸው ዛፎች፣ የቆሻሻ ማስወገጃ እና የአጥር ግንባታዎች ጥንቃቄ ካልተደረገባቸው ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትሉ እንደሚችሉ ገልጸዋል፡፡

ህብረተሰቡም ይህንን በመገንዘብ ከውል ውጪ በሚያከናውናቸው ተግባራት የሌላውን ደህንነት አደጋ ላይ በመጣል  ተጠያቂነት ስለሚያስከተል  ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የካቲት 19/2011 ዓ.ም. ሌሊት ስምንት ሰዓት አካባቢ  በመቱ ከተማ ቀበሌ አንድ በደረሰ የግንብ አጥር መደርመስ አደጋ የአንድ ቤተሰብ አባል የሆኑ ሰባት ሰዎች ህይወት ማለፉን ኢዜአ ፖሊስ በምንጭነት ጠቅሶ በወቅቱ ዘገቦ ነበር፡፡

በወቅቱ በአደጋው በእንቅልፍ ላይ የነበሩ እናትና ስድስት ልጆቻቸው ሕይወት ወዲያውኑ ሲያልፍ ከመካከላቸውም አምስቱ ዕድሜያቸው ከ15 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊ ህጻናት ነበሩ፡፡

በከተማው በቀን ሥራ ቤተሰቦቹን ሲያስተዳድር የነበረው የቤቱ አባወራ  ከዓመት በፊት በሕመም ምክንያት ሕይወቱ ማለፉ ታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም