ዲፕሎማቶች የኢንቨስትመንት አማራጮችን የማስተዋወቅ ተግባራቸውን ማጠናከር አለባቸው -የሰላም ሚኒስትር

52

አዲስ አበባ የካቲት 23/2011 በውጭ አገራት የሚመደቡ የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች የአገሪቱን የኢንቨስትመንት አማራጭና መልካም ገጽታ ለማስተዋወቅ የሚያደርጉትን ጥረት ማጠናከር ይጠበቅባቸዋል ሲል የሰላም ሚኒስትር አስገነዘበ።

የኢሚግሬሽን፣ ዜግነትና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ በተለያዩ አገራት አዲስ ለተመደቡ 68 ዲፕሎማቶች በወሳኝ ኩነት ጉዳዮች ላይ አትኩሮ ያዘጋጀው ስልጠና ዛሬ ተጠናቋል። 

ስልጠናው በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን  የልደት፣ የሞት፣ የጋብቻና ፍቺ  ህጋዊ ሰነድ አገልግሎትን ባሉበት ቦታ የሚያገኙበትን አመቺ አሰራር ለመፍጠር የሚያስችል ነው። 

ከዚህ በፊት በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን የሚሰጠው የወሳኝ ኩነት አገልግሎት በቂ አልነበረም ነው የተባለው።

በስልጠናው መዝጊያ ስነ-ስርዓት ላይ ሚኒስትር ዲኤታው አቶ ዘይኑ ጀማል እንዳሉት ዲፕሎማቶች በተለይ አሁን በአገሪቱ የተጀመረውን የለውጥ ሂደት፣ መልካም የምጣኔ ኃብትና ኢንቨስትመንት እድሎች  በማስተዋወቅ ረገድ ሰፊ ስራ ይጠበቅባቸዋል።

በተለይም በውጭ ለሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና የውጭ ባለኃብቶች መረጃን ጨምሮ ተገቢውን አገልግሎት በመስጠት ረገድ ዲፕሎማቱ የተጣለበት ኃላፊነት ከፍተኛ መሆኑንም ገልፀዋል። 

የኢሚግሬሽን ፣ ዜግነትና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙጂአብ ጀማል በበኩላቸው ዲፕሊማቶቹ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ከዜግነት ጋር ተያይዞ ለሚጠይቁት የወሳኝ ኩነት አገልግሎት ፈጣንና ጥራቱን የጠበቀ ምላሽ መስጠት አለባቸው።

የኢትዮጵያ መንግስትን በመወከል ለመጪዎቹ ሶስት ዓመታት በተለያዩ የውጭ አገራት የተመደቡት እነዚህ ዲፕሎማቶች የተጣለባቸውን ኃላፊነት በብቃት መወጣት ይችሉ ዘንድ አስፈላጊው ስልጠና እንደተሰጣቸው በዚሁ ወቅት ተገልጿል። 

አምባሳደሮችን ጨምሮ በኢትዮጵያ መንግስት በተለያየ የዓለም ክፍል የሚመደቡ ዲፕሎማቶች ግንባር ቀደም ተልእኮ የአገሪቱን ምጣኔ ኃብት፣ ኢንቨስትመንት፣ ንግድና መልካም ገፅታን በማስተዋወቅ  ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንትን ማጠናከር ነው።

ሆኖም የኢትዮጵያ ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንት በአሁኑ ወቅት በሚፈለገው መጠን እያደገ አለመሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ። 

ባለፈው የአውሮፓ ዓመት እንኳ አገሪቱ ከውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ያገኘቸው 3 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር ሲሆን ይህም ከዕቅዱ ያነሰ እንደሆነ ከኮሚሽኑ የተገኘ መረጃ አመልክቷል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም