አገልግሎት እየሰጡ ያሉ ባቡሮች ቁጥር ከዕለት ዕለት እየቀነሰ ነው -ተጠቃሚዎች

78
አዲስ አበባ ግንቦት 22/2010 የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር የተጠቃሚ ቁጥር እየጨመረ ሲሄድ  አገልግሎት እየሰጡ ያሉ ባቡሮች ቁጥር ከዕለት ዕለት እየቀነሰ መሆኑን ተጠቃሚዎች ይናገራሉ። የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንዚት አገልግሎት ድርጅት በበኩሉ  "ባቡሮቹ ዓመታዊ ፍተሻ ላይ ናቸው" በቅርቡ ወደ ስራ ሲገቡ ችግሩ በጥቂቱም ቢሆን ይቃለላል ብለዋል። ተጠቃሚዎቹ እንደሚሉት በተለይ በስራ መግቢያና መውጫ ሰዓት የባቡሮቹ በሮች በሰው መጨናነቅ  ምክንያት ዛሬም በትግል ነው የሚዘጉት። አገልግሎት መስጠት ሲጀምር 41 ፉርጎዎች ወደ ስራ እንደሚገቡ የተነገረ ቢሆንም አሁን ላይ ግን በተጨባጭ ሕብረተሰቡን የሚያመላልሱት ከግማሽ በታች ናቸው። በተጨማሪ የባቡሩ ምልልስ በየ6 ደቂቃ እንደሚሆን የተነገረ ቢሆንም አሁን በለው ሁኔታ እስከ  30 ደቂቃና ከዚያም በላይ የሚቆዩበት ጊዜ አለ፤ በዚህም ምክንያት ተሳፋሪውን አላረካም ያሉን የባቡር ተጠቃሚው አቶ መሃመድ አልዩና አቶ ተክላይ አስመላሽ ናቸው። በከተማው እየተባባሰ ላለው የትራንስፖርት እጥረት የባቡር ትራንስፖርት ከፍተኛ አማራጭ እንደሆነ ተማሪ ላምሮት ግርማ ትናገራለች። በተለይ ታክሲ ስንጠብቅ የትምህርት ቤት የመግቢያ ሰዓት እያለፈ ብዙ ችግሮች ገጥመዋት እንደነበር ነው የምትናገረው። በሰዓት ለመድረስ የባቡር አማራጭ ጥሩ ቢሆንም በሰው መብዛት የተነሳ ትኬት ቆርጣ ሳትሳፈርባቸው የቀረችባቸው ጊዚያቶች ብዙ እንደነበሩም ተናግራለች አቶ አማረ ወርቁ በስራ መግቢያና መውጫ ሰዓት የተሳፋሪ ቁጥር ስለሚጨምርና ስራ አርፍዶ  ስለሚገባ ከአሰሪዎቹ ጋር እያጋጨው መሆኑን ይናገራል። በተለይ አገልግሎት እየሰጡ ያሉ ባቡሮች ቁጥር ማነስ ችግሩን አባብሶታል ብለዋል። አሁን ባለው አካሄድ በየተሳፋሪዎች መጫኛና ማውረጃ በአማካኝ በ15 ደቂቃ የሚደርስ ሲሆን በየስድስት ደቂቃ የተባለው የረጅም ጊዜ ዕቅድ መሆኑን የድርጅቱ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ አወቀ ሙሉ ይናገራሉ። ነገር ግን በባቡር መሰረተ ልማቶች ላይ በሚደርሱ የተለያዩ አደጋዎች ከተያዘውም ሰዓት ዘግይተው ሊደርሱ ይችላሉ ብለዋል። በአሁኑ ወቅት ከ25 አስከ 26 ባቡሮች አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ። በቅርቡ ፍተሻቸውን ጨርሰው ወደ ስራ የሚገቡ ስድስት ባቡሮች ስለሚኖሩ ችግሩን በቀላሉም ቢሆን ይፈተዋል ብለዋል። ቀሪዎቹ ባቡሮች  ግን ለመጠባበቂያነት የምንጠቀምበት ነውም ይላሉ።  መንግስት በተያዘው ሁለተኛ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ 20 ባቡሮችን ለመግዛት ዕቅድ ያለው ሲሆን ይህንን ለማከናወን የሚያስችሉ ስራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውም ታውቋል። በተገኘው መረጃም የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር በአሁኑ ወቅት በቀን ከ115 እስከ 120 ሺህ ሰዎችን  የጓጉዛል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም