ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የአድዋን ታሪክ ለሀገራዊ አንድነት በሚያጠናክር አግባብ ማስተዋወቅ እንደሚጠበቅባቸው ተገለጸ

88

ሰመራ የካቲት 23/2011 ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እየተዘነጋ የመጣውን የአድዋ ድል ታሪክ ለሀገራዊ አንድነትና መግባባትን በሚያጠናክር አግባብ ለትውልዱ ማስተዋወቅ እንደሚጠበቅባቸው በሰመራ ዩኒቨርስቲ መምህራን ገለጹ፡፡ 

መምህራኑ ለኢዜአ እንዳሉት  የአድዋ ድል የኢትዮጵያዊያን አንድነትና ሀገር ወዳድነት  በተግባር ያረጋገጠ አኩሪ ገድል ነው፡፡

በተቋሙ የሲቪክስና እና ስነ-ዜጋ ትምህርት ክፍል መምህር አቶ እስጢፋኖስ በሰጡት አስተያየት ኢትዮጵያዊያን ጀግኖች በአድዋ በወራሪው ላይ ድል በመቀዳጀት የነጮች የበላይነት የቀየረ ታሪካዊ ገድል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዚህም  አፍሪካዊያን ለነጻነታቸውን ታግለው ማሸነፍ  እንደሚችሉ መነቃቃትን የፈጠረ መሆኑን ጠቅሰው  ይህን ታላቅ ድል ባለፉት ዓመታት በኢትዮጵዊያን ዘንድ የሚሰጠው ክብርና ቦታ እየተቀዛቀዘ መምጣቱን አመልክተዋል፡፡

የአድዋ ድል የድፍን ኢትዮጵያዊያን በመሆኑ ይህን አኩሪ ተግባር ተንከባክቦ እንዲጠበቅ ብሎም ለትውልድ እንዲተላለፍ በማሳወቅ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡ 

ሌላው የዩኒቨርስቲው መምህር አቶ ንጉሱ ታረቀኝ በበኩላቸው "የአለም ህዝብን ያስገረመው የአድዋው ታሪካዊ የጀግንነት ገድል አሁን ያለንበትን ሀገራዊ ሁኔታ ለመቀየር ያለውን ገንቢ ሚና ዘንግተናል" ብለዋል፡፡

አቶ ንጉሱ እንዳሉት ትናንትን በመቃወምና በመውቀስ ላይ የተቃኘ ፖለቲካዊ ርዕዮተ አለም የአድዋን ድል  ትውልዱ የራሱና  የአያቶቹ ታሪካዊ ውርስ መሆኑን እንዲጠራጠር አድርጎት ቆይቷል፡፡

ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ትውልዱን  በእውቀት በማነጽ ስህተቶች በፍጥነት እንዲታረም የድርሻቸውን መወጣት አለባቸው፡፡ 

የአድዋ ድል ለአለም ከማስተዋወቅ ባለፈ ኢትዮጵያ ነጻነቷን አስከብራ በማስቀጠል ትውልዱ እንዲታነጽ  ጉልህ አስተዋጽኦ ማድረጉን የገለጹት ደግሞ በዩኒቨርስቲው የታሪክ መምህር  ታሪኩ ዘነበ ናቸው፡፡

የኢትዮጵያዊያን አንድነትና ሀገር ወዳድነት  በተግባር ያረጋገጠው ይህኑ አኩሪ ገድል ጠብቆ ለትውልድ ለማስተላለፍ መሰራት እንዳለበት አስተያየት ሰጪዎቹ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም