ኬኒያ በምስራቅ አፍሪካ አንድነት እንዲመጣ ከኢትዮጵያ ጋራ በትብብር ትሰራለች_ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ

116

ደብረ ብርሃን የካቲት 23/2011 በምስራቅ አፍሪካ አንድነት እንዲመጣ ኬኒያ ከኢትዮጵያ ጋራ በመተባበር እንደምትሰራ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬኒያታ ገለፁ።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድና የኬንያው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ የደብረ ብርሃን ኢንዱስትሪ ፓርክን ዛሬ በጋራ መርቀዋል።

በዚሁ ወቅት የኬንያው ፕሬዝዳንት እንደተናገሩት ኢትዮጵያና ኬንያ ያላቸውን የጋራ እሴቶች ለማስቀጠል በቅንጅት ይሰራሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በሀገር ውስጥ የሚያስተላልፉት የአንድነት መልዕክት ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለቀጠናውም ጠቃሚ ነው ብለዋል።

"በቀጠናው ያለን ሀገርና ሰዎች አንድ ነን"፤ በጋራ በመሆን ድህነትን በማጥፋት እድገትን ማስቀጠል ይገባል" ሲሉ ነው ፕሬዚዳንት ኬንያታ ያስገነዘቡት።

ያም ብቻ ሳይሆን አንድነት ለሁሉም ስኬቶች መፍትሄ መሆኑን ጠቁመው በየትኛውም አቅጣጫ የሚመጣውን ጠላት ማሸነፍ ይቻላል ብለዋል።

በመሆኑም ኬንያ ከኢትዮጵያ ጎን በመቆም በምስራቅ አፍሪካ አንድነት እንዲመጣ እንደምትሰራ ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትሯ አማካኝነት ቀጣናውን ለማስተሳሰር እያደረገች ያለውን ሚና ፕሬዝዳንት ኬኒያታ አድንቀዋል።

የኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ በኢትዮጵያ ይፋዊ የስራ ጉብኝት ለማድረግ አዲስ አበባ የገቡት ትናንት ነው።

በጉብኝታቸው ወደ ደቡብ ክልል በመጓዝ የሐዋሳ ኢንዱስተሪ ፓርክንና የአርባምንጭ ተፈጥሯዊ መስህቦችን ጎብኝተዋል።

የጋሞ ጎፋ የሃገር ሽማግሌዎች የአድዋ የድል በዓልን  ምክንያት በማድረግ ፤ በጋሞ ጎፋ ሽማግሌዎችም የፈረስ፣ ጦርና ጋሻ ስጦታ ተበርክቶላቸዋል። 

የኢትዮጵያና ኬንያን  የምጣኔ ኃብትና ኢንቨሰትመንት ግንኙነት ማጠናከር በሚቻልበት መንገድ ላይ ለመምከር በአዲስ አበባ በተካሄደው ፎረም ላይም ፕሬዚዳንቱና ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ተሳትፈዋል።

ከፎረሙ ባሻገር ከፕሬዚዳንቱ ጋር ወደአዲስ አበባ የመጡት ከ100 በላይ የአገሪቱ ባለኃብቶችና ኩባንያ ተወካዮች ከኢትዮጵያዊያን አቻዎቻቸው ጋር በጋራ መስራት በሚችሉበት መንገድ ላይ ይወያያሉ ተብሏል። 

ዛሬ ከቀትር በኋላም ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ከፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ጋር በአገራቱ የጋራ ጉዳዮች ዙሪያ ይመክራሉ ተብሎ ይጠበቃ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም