ወጣቱ ከመከፋፈልና ከጥላቻ ርቆ ሀገሩን መገንባት አለበት...ዶክተር አብይ አህመድ

110

ደብረብርሃን የካቲት 23/2011 ወጣቱ ትውልድ ከአድዋ ድል በመማር ከመከፋፈልና ከጥላቻ ርቆ ለሃገር ግንባታ በጋራ መስራት እንዳለበት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አሳሳቡ።

በ75 ነጥብ አራት ሚሊዮን ዶላር የተገነባው የደብረ ብርሀን ኢንዱስትሪ ፓርክን ጠቅላይ ሚኒስትሩና የኬኒያው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ በተገኙበት ተመርቋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት የበለፀገች ዜጎቿ የሚተማመኑባት የአፍሪካ ብሎም የአለም ኩራት የሆነች ኢትዮጵያን ለመገንባት በፍቅርና በአንድነት መተሳሰርን ከአድዋ አባቶች መማር ይገባል።

ለኢትዮጵያ አንድነትና ሰላም መረጋገጥ ሁሉም ህዝቦች በአንድነት ለመስራት የበለፀገች ዜጎቿ የሚተማመኑባት የአፍሪካ ብሎም የአለም ኩራት የሆነች ኢትዮጵያን ለመገንባት በፍቅርና በአንድነት መተሳሰርን ከአድዋ አባቶች መማር ይገባል ብለዋል፡፡

በቀጣይ ዓመታት ሀገሪቷን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ሰላምና ዴሞክራሲን ለማስፈን በሚደረገው ያልተቆጠበ ጥረት ህዝቡ በጋራ ሊሰራ እንደሚገባም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡

ወጣቱ በተገነቡና ወደ ስራ በመግባት ላይ ባሉ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ለመስራት ከተለያየ የዓለም ክፍል ከሚመጡ ባለሃብቶች መልካም ልምዶችን ወስዶ በመስራት የራሱን ሃብት የሚያፈራበት እድል መፍጠር እንደሚጠበቅበት ተናግረዋል።

የኢፌዴሪ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽን ስራ አስፈፃሚ ወይዘሪት ሌሊሴ ነሜ እንደገለጹት በኢንዱስትሪ ፓርኩ አንድ ሺህ 100 ሄክታር መሬት ውስጥ የተገነቡት ስምንት የማምረቻ ሼዶች ናቸው።

ግንባታው በ2009 ዓ.ም ተጀምሮ ዛሬ ለምረቃ የበቃው ኢንዱስትሪ ፓርኩ በጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪው ዘርፍ እሴት የተጨመረባቸውን አልባሳት ወደ ውጭ በመላክ በትኩረት እንደሚሰራ አስረድተዋል።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በበኩላቸው በልማት ወደ ኋላ ቀርቶ የነበረው የደብረ ብርሃን ከተማና አካባቢው አሁን በፈጣን የእድገት ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡

ከዚህ ቀደምም የኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ ስራ መጀመሩን ጠቁመው የባህር ዳርና የቡሬ ኢንዱስትሪ ፓርኮችም በግንባታ ላይ መሆናቸውን አስታውሰዋል።

እነዚህ ፓርኮች ሙሉ በሙሉ ወደ ማምረት ሲገቡም የክልሉን ህዝብ ተጠቃሚ በማድረግ ለድህነት ቅነሳው ጉልህ ሚና እንደሚኖራቸው ገልፀዋል።

በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ የኬኒያው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ አመራሮችና የአካባቢው ህዝብ ተገኝቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም