የወሊሶ ደም ባንክ አራት ሺህ ዩኒት ደም ሰበሰበ

62

አምቦ የካቲት 23/2011 የወሊሶ ደም ባንክ አራት ሺህ  ዩኒት ደም ከበጎ ፈቃደኞች በልገሳ ማግኘቱን ገለጸ።

ደም በመለገስ ሕይወት የማዳን ተግባር ስራ እንደሚያጠናክሩ ለጋሾች ተናግረዋል።

የወሊሶ ደም ባንክ ኃላፊ አቶ ሸለመ ጎንፋ ለኢዜአ እንደገለጹት ከበጎ ፈቃደኞች ደም በበጀት ዓመቱ ለመሰባሰብ ከተያዘው 7ሺህ ዩኒት ደም ውስጥ ነው፡፡

ደም የለገሱት በምዕራብና ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ፣በሰሜን ሸዋና በአዲስ አበባ ልዩ ዞን ከሚገኙ የሁለተኛ ደረጃና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች እንዲሁም መንግሥታና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅት ሠራተኞች ናቸው ብለዋል ፡፡

የተሰበሰበው ደም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ100 ዩኒት ብልጫ አለው፡፡

ብልጫው የተመዘገበው የኅብረተሰቡ ደም የመለገስ ባህል እየዳበረ በመምጣቱ ነው ብለዋል።

ተጠቃሚ ከሆኑትም በወሊድ የተጎዱ እናቶች፣ ህጻናትና የትራፊክ አደጋ የደረሰባቸው ሰዎች ይገኙበታል፡፡

ከበጎ ፈቃደኞች የተሰበሰበው ደም ለ12 ሆስፒታሎች መሰራጨቱን ኃላፊው  አስረድተዋል።

የኤጀሬ ወረዳ ነዋሪ አቶ ፍቀረ ኡማ ደም መለገስ በድንገተኛ ለአደጋ የሚጋለጡ ሰዎችን ሕይወት ለመታደግ ለሁለተኛ ጊዜ መለገሳቸውን ተናግረዋል፡፡

ለመጀመሪያ ጊዜ ደም መለገሳቸውን የገለጹት ደግሞ ወይዘሪት ባጩ በርሲሳ ናቸው።

በአምቦ ዩኒቨርሲቲ ሪፈራል ሆስፒታል ሶስተኛ ልጃቸውን የተገላገሉት ወይዘሮ ገነት ደምሴ በሰጡት አስተያየት የደም እጥረት አጋጥሟቸው ከባንኩ ባገኙት ደም አገልግሎት ሕይወታቸው መትረፉን ገልጸዋል።

ደም በመለገስ የአናቶችንና የሕጻናትን ሕይወት ለታደጉ በጎ ፍቃደኞች ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

ባንኩ ባለፈው ዓመት 4 ሺህ 800 ዩኒት ደም በመሰብሰብ ለተጎጂዎች መስጠቱ አስታውሷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም