የደቡብ ሱዳኑ ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር አዲስ አበባ ገቡ

94
አዲስ አበባ  ግንቦት 22/2010 የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ማያርዲት ዛሬ አዲስ አበባ ገብተዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ አዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ጣቢያ በመገኘት ፕሬዝዳንቱን ተቀብለዋቸዋል። ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ከጠቅላይ ሚኒሰተር ዶክተር አብይ አህመድ ጋር በመገናኘት በደቡብ ሱዳን  ሰላም ለማምጣት እየተካሄደ ባለው ጥረት ዙሪያ ውይይት ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል። የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) የሚኒስትሮች ምክር ቤት በደቡብ ሱዳን የሰላም ጉዳይ ላይ ለመምከር በዚሁ ሳምነት አዲስ አበባ ውስጥ ይሰበሰባል ተብሏል። በአገሪቱ የፖለቲካ ተቀናቃኞች መካከል የተከሰተውን አለመግባባት ተከትሎ ላለፉት አምስት ዓመታት የዘለቀው የእርስ በርስ ጦርነት በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ህይወት ቀጥፏል፤ ከአራት ሚሊዮን የሚልቁት ደግሞ ከቀዬአቸው እንዲፈናቀሉና ኢትዮጵያን ጨምሮ ወደጎረቤት አገራት እንዲጠለሉ አስገድዷል። በዚህች አገር ሰላም እንዲመጣ ኢጋድ ቁልፍ ሚና በመጫወት ላይ መሆኑ ይታወቃል። ለደቡብ ሱዳን ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ባለፈው ሳምንት በኢጋድ አማካኝነት አዲሱ የሰላም ሀሳብ መቅረቡም ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም