ወጣቱ ትውልድ ከአድዋ ድል የሃገር ሉዓላዊነት የማክበር ጽናትን መማር አለበት ተባለ

74

አክሱም የካቲት 23/2011 "ወጣቱ ትውልድ ከአድዋ ድል ቀደምት አያቶቹ የሃገር ሉዓላዊነት የማክበር ጠንካራ ተጋድሎና ጽናትን መማር አለበት " ሲሉ የአክሱም ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ፀሐዬ ወልደሚካኤል ገለጹ።

123ኛ የአድዋ ድል በዓልን ምክንያት በማድረግ በአድዋ ከተማ የፓናል ውይይት ተካሂዷል።

ዩኒቨርስቲው ከአክሱም ከተማ አስተዳደር ጋር በመተባበር ባዘጋጀው ውይይት ላይ ዶክተር ፀሐዬ እንዳሉት ፣ ኢትዮጵያ በጣሊያን ወራሪ ኃይል ሳትወረር ነጻነቷን አስከብራ  የኖረችው በቀደምት አያቶቻችን የተጋድሎ ጽናት  ነው።

ቀደምት ኢትዮጰያዊያን ለሃገራቸው ከነበራቸው ቀናኢነት የተነሳ በከፈሉት መስዋእትነት ሉዓላዊነቷን ሳይደፈር ተከብራ እንድትኖር ማስቻላቸውን አመልክተዋል።

"የአሁኑ ወጣት ከቀደምት አያቶቻቸው የሃገር ሉዓላዊነትን የማስከበር ጠንካራ ተጋድሎና ጽናትን መማር አለበት"ብለዋል፡፡

በዝግጅቱ  በሁለት የአክሱም ዩኒቨርስቲ የታሪክ ምሁራን" የአድዋ ጦርነት አጀማመርና ለአውሮፓውያን የሰጠው ትምህርት"  በሚል ርዕስ የመወያያ ጽሑፍ ቀርበዋል።

ከጸሁፍ አቅራቢ ምሁራን መካከል ዶክተር ተክለኃይማኖት ገብረ ስላሴ እንዳመለከቱት የአድዋ ጦርነትና ድል የውጭ ወራሪ ኃይሎች የጥቁር ህዝቦችን  ድል አድራጊነት በተግባር እንዲማሩ አስገድዷቸዋል።

"ድንቅ የታሪክ ስፍራዎቹ ለዘላለም እንዲታሰቡ ለማድረግ ዘመናዊ ሙዚዬም በመገንባት በጦርነቱ የነበሩት ቅርሶችን በመሰብሰብ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ማድረግ ይገባል" ብለዋል።

በስፍራዎቹ ሀውልቶችን በማቆም ለቱሪዝም ልማት እንዲውሉ ማድረግም እንደሚገባ አሳስበዋል።

በውይይቱ ከተሳተፉት ውስጥ  መምህር ሙሉወርቅ ኪዳነማርያም በሰጡት አስተያየት የአድዋ ድልን ለማስታወስ በየዓመቱ ቢከበርም የበዓሉን ክብር ለማጉላት የሚሰሩ ተግባራት ዝቅተኛ መሆኑን ተናግዋል።

የአድዋ ጦርነት የተካሄደበት ስፍራ እና የተሰሩት  ድንቅ ታሪኮችን ለቀጣይ ትውልድ ለማስተላለፍ በስርዓተ ትምህርት ውስጥ ተካቶ በመደበኛ የትምህርት ፕሮግራም እንዲሰጥ መልክታቸውን አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም