የአድዋ ድል "የአፍሪካ የነጻነት ትግል የተጠነሰሰበት ዕለት ነው" - ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ

240

አርባ ምንጭ የካቲት 23/2011 ኢትዮጵያዊያን ጣሊያንን በአድዋ ጦርነት በማሸነፍ አንጸባራቂ ድል ያስመዘገቡበት ቀን "የአፍሪካውያን የነጻነት ትግል የተጠነሰሰበት ዕለት ነው" ሲሉ የኬንያ ፕሬዚዳት ኡሁሩ ኬንያታ ገለጹ።

ከትናንት ጀምሮ ይፋዊ የስራ ጉብኝት በማድረግ ላይ የሚገኙት ፕሬዚዳንት ኬንያታ የአድዋ ድል የአፍሪካውያን ኩራት መሆኑን ተናግረዋል።

በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በአርባ ምንጭ ከተማ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እና ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ጉብኝት እያደረጉ ነው።

የጋሞ አገር ሽማግሌዎች የአድዋን ድልን ምክንያት በማድረግ ለሁለቱም መሪዎች ለእያንዳንዳቸው የፈረስ ፣ ጋሻና ጦር ስጦታ አበርክተውላቸዋል።

መሪዎቹ የአገር ሽማግሌዎቹን ስጦታ ከተረከቡ በኋላ ፕሬዚዳንት ኬንያታ በምስጋና ንግግራቸው ፤ የአድዋ ድል አፍሪካውያንን ለትግል ያነቃቃ መሆኑን ገልጸዋል።

በ1888 ዓ.ም በየካቲት የጣሊያን የቅኝ ግዛት ተስፋፊ ጦር ድል ከተነሳ በኋላ አፍሪካውያን መነቃቃታቸውንና ለነጻነት ትግል መነሳሳታቸውን ታሪክ ያወሳዋል።

ድሉ ለፓን አፍሪካን ንቅናቄ ስኬት መሠረት መጣሉን የሚገልጸውን ሀሳብ  ነው የፕሬዚዳንቱ ገለጻ የሚያጠናክረው።

በአድዋ ጦርነት የተመዘገበው ድል "የአፍረካ ነጻነት ትግል ተጠንስሶበታል" ያሉት ፕሬዚዳንት ኬንያታ፤ ድሉ አፍሪካውያን ወደ አንድነት ለሚያደርጉት ጉዞ መነቃቃትን የፈጠረ መሆኑንም አጽንኦት ሰጠውታል።

በአሁኑ ወቅት  ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የቀጣናውን አካባቢ አንድ ለማድረግ እያከናወኑ ያለውን ተግባርም አድንቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በበኩላቸው፤ የአድዋ ድል "ጀግኖች አባቶቻችን ለአንድነት የከፈሉት መስዋዕትነት ነው" ብለዋል።

ኢትዮጵያዊያን ከመገፋፋት መውጣትና አቃፊ መሆን እንደሚገባቸው አጽንኦት የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በዚህ ወቅትም የአድዋ ድል ድርብ ድል እንደሚሆን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት ዜጎች በአንዳንድ አካባቢዎች የሚነሱ ችግሮችን በመስማት መደናገጥ እንደሌለባቸው ጠቁመው፤ በአድዋ ድል መንፈስ የበለጠ ለአንድነታቸው መስራት እንደሚጠበቅባቸው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያዊያን ጣሊያንን ድል ካደረጉበት ማግስት ጀምሮ ጥቁር ህዝቦች ለነጻነት ትግል መነቃቃታቸውና አመርቂ ውጤት ማስመዝገባቸው የታሪክ ድርሳናት አስፈረውታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም