በዞኑ አዲስ የተቋቋሙ 37 ኢንዱስትሪዎች ማምረት ጀመሩ

86

ሽሬ እንዳስላሴ የካቲት 22/2011 በትግራይ ሰሜናዊ ምዕራብ ዞን አዲስ የተቋቋሙ 37 የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች ማምረት መጀመራቸውን የዞኑ አስተዳደር አስታወቀ።

ኢንዱስትሪዎቹ ለ2 ሺህ 500 ነዋሪዎች የስራ እድል መፍጠራቸውም ተነግሯል።

የዞኑ መስተዳድር የከተሞች ልማት ጉዳዮች አማካሪ አቶ ሙላው ይሳቅ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ስድስት ወራት 1 ቢሊዮን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሀብቶች በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ተሰማርተዋል።

ከባለሀብቶቹ መካከል 93ቱ በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዘርፍ የተሰማሩ መሆናቸውን ጠቅሰው በዘርፉ ከተሰማሩ ባለሀብቶች መካከል 37ቱ ያቋቋሟቸው ኢንዱስትሪዎች ወደምርት መግባታቸውን ገልጸዋል።

አብዛኛዎቹ ኢንዱስትሪዎች በሚስማርና ቆርቆሮ፣ ፕላስቲክና የኃይል ተሸካሚ ኮንክሪት ምሰሶ ማምረት ሥራ ላይ ያተኮሩ መሆናቸውን የገለፁት አማካሪው ኢንዱስትሪዎቹም ለ2ሺህ 500 ሰዎች ቋሚ የሥራ እድል መፍጠራቸውን ተናግረዋል።

በግንባታ ሂደት ላይ ባሉ 56 አምራች ኢንዱስትሪዎችም ከ10 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ነዋሪዎች ጊዜያዊ የሥራ እድል መፈጠራቸውን ጨምረው ገለፀዋል ።

በኢንዱስተሪዎቹ የሥራ እድል የተፈጠረላቸው አስተያየት ሰጪዎች በበኩላቸው "እያገኘን ባለነው ገቢ ራሳችንን ችለን ቤተሰቦቻችንን መርዳት ችለናል" ብለዋል ።

ወጣት ሲሳይ ንጉሰ እንዳለው በተማረው የመካኒካል ኢንጂነሪንግ ሙያ ተቀጥሮ ራሱንና ቤተሰቡን በማስተዳደር ላይ መሆኑን ተናግሯል።

"በተማርኩት የሒሳብ ስራ ሙያ የሥራ እድል በማግኘቴ ሁለተኛ ዲግሪዬን ለመቀጠል እድል አግኝቺያለሁ" ያለችው ደግሞ ወጣት ጸሐይነሽ አለሙ ናት።

በኢንጂነሪንግ ሙያ የተመረቀው ወጣት ተስፋይ ጠዓመ በበኩሉ "በተቀጠርኩበት የግል ማምረቻ በማገኘው ደመወዝ ቤተሰቦቼን መርዳት በመጀመሬ ደስታኛ ነኝ” ብሏል ።

ከዞኑ አስተዳደር የተገኘ መረጃ እንደሚያሳየው በዞኑ ባለፉት ስድስት ወራት በግል ባለሃብቶች ከተፈጠረው የሥራ ዕድል በተጨማሪ በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች 5 ሺህ 700 ወጣቶች የሥራ እድል ተጠቃሚ ሆነዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም