የአድዋ ድል በዓል በሰላም እንዲከበር ለማድረግ ዝግጅት ተጠናቋል - የአዲስ አበባ የፀጥታ ምክር ቤት

69

አዲስ አበባ የካቲት 22/2011 የአድዋ ድል በዓል በሰላም እንዲከበር ለማድረግ ዝግጅት ማጠናቀቁን የአዲስ አበባ ከተማ የፀጥታ ምክር ቤት አስታወቀ።

በዓሉ ነገ በአዲስ አበባ ዳግማዊ ምኒልክ አደባባይና በተለምዶ አዋሬ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሚገኘው የአድዋ ድልድይ ይከበራል።

የከተማዋ የፀጥታ ምክር ቤት የበዓሉን አከባበር አስመልክቶ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር የቅድመ ዝግጅት ሥራ ማጠናቀቁን ከከንቲባ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የከተማ አስተዳደሩ በዓሉን በደመቀ ሁኔታ ለማክበርና የኀብረተሰቡን ደህንነት ለመጠበቅ አስፈላጊውን ዝግጅት ማጠናቀቁን አስታውቋል።

በዕለቱ በዓሉን ለሚያከብሩ የከተማዋ ነዋሪዎች ሸገር የብዙሃን ትራንስፖርት አገልግሎት ነጻ የትራንስፖርት አገልግሎት እንደሚሰጥ ተገልጿል።

ከቂርቆስና ከቦሌ ክፍለ ከተሞች የሚመጡ የበዓሉ ታዳሚዎች የደንበልን፣ ከንፋስ ስልክና አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተሞች የሚመጡ የጎተራ-ሪቼ፣ ከኮልፌና ልደታ ክፍለ ከተሞች የሚመጡ ደግሞ የለገሃርን መንገዶች እንዲጠቀሙ ተነግሯል፤

ከአዲስ ከተማና ከጉለሌ ክፍለ ከተሞች የሚመጡ የበዓሉ ታዳሚዎች ደግሞ የፒያሳ-ጊዮን መንገድን እንዲጠቀሙ ጠይቋል።

በተጨማሪም ከኮልፌና ጉለሌ ክፍለ ከተሞች እንዲሁም ከአራዳና የካ ክፍለ ከተሞች የሚመጡ የበዓሉ ታዳሚዎች በግቢ ገብርኤል-ኢ.ሲኤ መንገድ እንዲጠቀሙ ያስታወቀ ሲሆን ለበዓሉ ታዳሚዎች ሲባል የተጠቀሱት መንገዶች ለትራፊክ ዝግ ይሆናሉ ብሏል። 

የመዲናዋ ነዋሪዎች ሌሎች አማራጭ መንገዶችን እንዲጠቀሙና የበዓሉ ታዳሚዎች በተገለጹት መንገዶች ብቻ እንዲጠቀሙም ጥሪ አቅርቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም