በቅርጫት ኳስ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ወልቂጤ ከተማ ቢጂአይ ኢትዮጵያን አሸነፈ

72

አዲስ አበባ  የካቲት 22/2011በኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ ወልቂጤ ከተማ ቢጂአይ ኢትዮጵያን አሸንፏል።

በምድብ አንድ በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም በተደረገው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ወልቂጤ ከተማ ተጋጣሚውን 51 ለ 37 በሆነ ውጤት ረቷል።

ውጤቱንም ተከትሎ ወልቂጤ ከተማ ነጥቡን ወደ ስድስት ከፍ በማድረግ የምድብ መሪነቱን ያጠናከረ ሲሆን በአንጻሩ ቢጂአይ ኢትዮጵያ ሶስት ነጥብ በመያዝ የመጨረሻው ሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

የምድብ አንድ ቀሪ መርሃ ግብሮች በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም የሚካሄዱ ይሆናል።

ነገ አማራ መንገድና ህንጻ ዲዛይን ከቢጂአይ ኢትዮጵያ፣ ከነገ በስቲያ አማራ መንገድና ህንጻ ዲዛይን ከወልቂጤ ከተማ በተመሳሳይ ከጠዋቱ በ3፡00 ሠዓት ይጫወታሉ።

በኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን አዲስ የውድድር ፎርማት መሠረት በሊጉ በምድብ አንድ የተደለደሉት ሦስት ክለቦች ወደ አዲስ አበባ በማምራት ለሦስት ተከታታይ ቀናት ጨዋታቸውን ያካሂዳሉ።

በዚሁ መሰረት ወልቂጤ ከተማ ከቢጂአይ ኢትዮጵያ የተጫወቱ ሲሆን ነገና ከነገ በስቲያ በአዲስ አበባ በምድቡ ሁለት ጨዋታዎች ይደረጋሉ ማለት ነው።

በሌላ በኩል በሀበሻ ሲሚንቶ የወንዶች ፕሪሚየር ሊግ ከነገ በስቲያ ሁለት ተስተካካይ ጨዋታዎች ይካሄዳሉ።

ሶዶ ላይ የአምናው የፕሪሚየር ሊጉ አሸናፊ ወላይታ ድቻ ከአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ከቀኑ በ9፡00 ሠዓት ይጋጠማሉ።

የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በአንደኛ ሳምንት መካሄድ የነበረበት መርሃ ግብር ነው።

ባሌ ላይ መዳወላቡ ዩኒቨርሲቲ ከፌዴራል ማረሚያ ቤቶች የሰባተኛ ሳምንት ተስተካካይ ጨዋታቸውን የሚያደርጉ ይሆናል።

በፕሪሚየር ሊጉ በተለያዩ ምክንያቶች የተራዘሙ ጨዋታዎች በተስተካካይ መርሃ ግብር ከተከናወኑ በኋላ የሊጉ የመጀመሪያ ዙር የሚጠናቀቅ ይሆናል።

በሀበሻ ሲሚንቶ የወንዶች ፕሪሚየር ሊግ ስምንት ቡድኖች እየተሳተፉ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም