የሴፍትኔት መርሃ ግብር ተሳታፊዎች ኑሯቸው እየተሻሻለ መሆኑን ገለጹ

70

አዲስ አበባ  የካቲት 22/2011በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል የተለያዩ ወረዳዎች እየተካሄደ ያለው ልማታዊ ሴፍትኔት መርሃ-ግብር ተሳታፊ ዜጎች ህይወት እየተሻሻለ ነው ተባለ።

የመርሃ-ግብሩ ዓላማ ዜጎች በተፈጥሪና ሰው ሰራሽ ችግሮች ሳቢያ የተጋረጠባቸውን የምግብ ዋስትና ችግር መከላከል ይችሉ ዘንድ የገንዘብና ሌላ ድጋፍ በማድረግ ሰርተው ጥሪት እንዲያፈሩ ሁኔታዎችን ማመቻቸትና የምግብ ዋስትናቸውን እንዲያረጋግጡ ማስቻል ነው።

በአሁኑ ወቅት በመላው አገሪቱ 7 ነጥብ 9 ሚሊዮን ህዝብ በመርሃ ግብሩ እየተሳተፈ መሆኑንም መረጃዎች ይጠቁማሉ። 

በደቡብ ክልልም የመርሃ ግብሩ ተሳታፊ ዜጎች በተፈጥሮ ኃብት ጥበቃ፣ በአፈር እቀባ፣ በእርከን ሥራ፣ በከብት ማደለብና በተለያዩ የመሰረተ ልማት ዘርፎች ልማት በመሰማራት ላይ ናቸው።

ከተሳታፊዎቹ መካከል የሆኑት በክልሉ የኮንሶ ዞን ሰገማ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ቱሩፋት ቡሮ ገንዘብን ጨምሮ በመርሃ-ግብሩ በተደረገላቸው ድጋፍ ከተረጂነት ተላቀው ኃብት ማፍራታቸውን ተናግረዋል።

"ከዚህ በፊት የሴፍትኔት ተረጂ ነበርኩ፤ አሁን እራሴን ችያለው፤ ኑሮዬ ተሻሽሏል።" ብለዋል።

ሌላው ተጠቃሚ ወይዘሮ ሸኮ ገመቹ በበኩላቸው "ከዚህ በፊት የደሃ ደሃ ነበርኩ፤ አሁን ላይ በመርሃ -ግብሩ ባገኘሁት ድጋፍ ህይወቴ መሻሻል አሳይቷል" ይላሉ።

በዞኑ ግብርና ጽፅህፈት ቤት የምግብ ዋስትና ቡድን መሪ አቶ ካራሌ ቀሳሶ የሴፍትኔት በመርሃ-ግብሩ አማካኝነት ህዝቡን በተፋሰስ ስራ፣ የአካባቢ ጥበቃ፣ በዛፍ ተከላ፣ በአፈር ጥበቃ፣ በትምህርት ቤት ግንባታና የመሳሰሉ ልማት ሥራዎች በማሳተፍ ገቢያቸው እንዲጨምረ እያደረገ ነው። 

በዞኑ በ31 ቀበሌ ውስጥ የሚኖሩ 40 ሺህ 600 ሰዎች የልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮግራም ተጠቃሚ ሲሆኑ ከዚህ ውሰጥ ከ36 ሺህ  በላይ የሚሆኑት በተለያዩ የልማት ስራዎች እየተሳተፉ በየዓመቱ ለ6 ወራት ክፍያ የሚፈጸምላቸው ናቸው።

መርሃ ግብሩ በችግር ውስጥ ያሉ ዜጎችን ህይወት ከማሻሻል ባለፈ የተፈጥሮ ኃብት ጥበቃን በማጎልበት የአካባቢውን ለምነተ መልሶ ማምጣትም እያስቻለ ነው የተባለው።

በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል የግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ መለስ መና በክልሉ የልማታዊ ሴፍትኔት ተጠቃሚዎች እራሳቸውን ከተረጂነት ለማውጣተ ከማስቻል ባሻገር የክልሉ የምግብ ዋስትና ለማሻሻል ለሚደረገው ጥረትም የበኩሉን አስተዋፅኦ እያበረከተ  መሆኑን ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ ስር የሰደደ የምግብ ዋስትና ችግር ያለባቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች ኑሮ በተለያየ መንገድ በመደገፍ ህይወታቸውን የመታደግ ዓላማ ያለው ልማታዊ ሴፍትኔት መርሃ-ግብር የተጀመረው የዛሬ 13 ዓመት ገደማ ነው። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም