ቦርዱ የሲቪክ ማህበራት በምርጫ ሂደት ያላቸውን ሚና ለማሳደግ ይሰራል

67

አዲስ አበባ የካቲት 22/2011 የሲቪክ ማህበራት በኢትዮጵያ የምርጫ ሂደት ያላቸውን ሚና ለማሳደግ እንደሚሰራ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ።

ቦርዱ የሲቪክ ማህበራት በምርጫ ሂደት በሚኖራቸው ሚናና በሚያጋጥሟቸው ተግዳሮቶች ላይ ዛሬ ተወያይቷል።

የቦርዱ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ እንዳሉት የሲቪክ ማህበራት የምርጫ ሂደትን በመታዘብና ለኀብረተሰቡ የስነ ዜጋ ትምህርት በመስጠት በኩል የማይተካ ሚና አላቸው።

ከዚህ ቀደም በተካሄዱ ምርጫዎች የሲቪክ ማህበራት የሚሰጡትን አገልግሎት የሚያጠቡና የሚገድቡ እንቅፋቶች እንደነበሩ አስታውሰዋል።

ቦርዱ በቀጣይ የሲቪክ ማህበራቱ በነጻነት እንዲንቀሳቀሱ ግልጽ ደንብና ስርዓት በማዘጋጀት ተዓማኒ የሆነ ምርጫ 'እንዲካሄድ ይሰራል' ብለዋል።

የዛሬው ውይይት ዓላማ የዜጎችን የጋራ ፍላጎት በማንጸባረቅና የምርጫውን ተዓማኒነት በማረጋገጥ ረገድ የሲቪክ ማህበራትን ሚና እውን ለማድረግ የሚስችሉ የዝግጅት ስራዎችን ለማከናወነ ነው።

የማህበራቱን ዝግጁነት፣ በምርጫ ቦርድ አሰራር ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለመቃኘትና መፍትሔ ለማበጀት የተካሄደ የመጀመሪያ ውይይት እንደሆነም ወይዘሪት ብርቱካን አስረድተዋል።    

የሰብዓዊ መብት ተሟጋችና የህግ ባለሙያ አቶ ዳንኤል በቀለ የሲቪክ ማህበራት ባለፉት ጊዜያት በቅድመ፣ በድህረና በምርጫ ወቅት  የነበራቸውንና ቀጣይ ሚናቸውን የተመለከተ ጽሁፍ አቅርበዋል።

የሲቪክ ማህበራት በአገሪቱ በተለይም በ1997 ዓ.ም ምርጫ ጠንካራ ጥምረት በመፍጠር ሂደቱ የተሻለ እንዲሆን ጥረት ማድረጋቸውን አውስተዋል።

የክርክር መድረኮችን በማዘጋጀት ኀብረተሰቡ ስለ ምርጫው የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖረው በማድረግና በምርጫ ታዛቢነት በተሳተፉባቸው በአዲስ አበባና ዙሪያዋ የተሻለ ምርጫ እንዲካሄድ ማድረጋቸውን አስታውሰዋል። 

ሆኖም ግን የምርጫ ታዛቢነታቸው በተለያዩ ምክንያቶች በመገደቡ በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች ምርጫውን መታዘብ አለመቻላቸውን ገልጸዋል።   

ከዚህ ቀደም በነበሩ የምርጫ ሂደቶች የማህበራቱ ተሳትፎ የተገደበና የተከፋፈለ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ያለውን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ኀብረተሰቡን ማገልገል እንደሚገባ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የአውሮጳ ህብረት ተጠሪ አምባሳደር ጆሀን ቦርግስተም በበኩላቸው የኢትዮጵያ መንግስት በቅርቡ የሲቪክና የበጎ አድራጎት ማህበራት አዋጅ ላይ ያደረገውን ማሻሻያ አድንቀዋል።

ማህበራቱ አገሪቱን በነጻነት ለማገልገልና ለመደራጀት ያገኙትን መልካም አጋጣሚ በአግባቡ ሊጠቀሙበት እንደሚገባም ገልጸዋል።

በተለይ በአገሪቱ የሚካሄደውን ምርጫ ሂደት ለማሻሻል በሚደረገው ስራ በመሳተፍ የተሻለ የምርጫ ስርዓት እንዲኖር የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱም ጥሪ አቅርበዋል። 

የአውሮጳ ኀብረትም የኢትዮጵያ የምርጫ ስርዓት የተሻለ እንዲሆን የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል።

የውይይት መድረኩን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከአውሮጳ ኀብረት ጋር አዘጋጅተውታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም