የኬንያና የኢትዮጵያ መሪዎች የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክን ጎበኙ

66

ሐዋሳ የካቲት 22/2011 የኬንያው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ዛሬ የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክን ጎብኝተዋል።

ፕሬዚዳንቱ ፓርኩን የጎበኙት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓቢይ አህመድና ከኬንያ የንግድ ማህበረሰብ ጋር በመሆን ነው።

መሪዎቹ በዚሁ ወቅት በፓርኩ የሥራ እንቅስቃሴ ላይ ያተኮረ ማብራሪያና ገለጻ ተደርጎላቸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ ባለፈው ዓመት በኬንያ ባደረጉት ጉብኝት በአገሮቹ መካከል ያለው የኢኮኖሚ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ መስማማታቸው ይታወሳል።

የፕሬዚዳንቱ ጉብኝት ስምምነቱን ከፍ ወዳለ ምዕራፍ ያሸጋግረዋል ተብሎ እንደታመነበት የፓርኩ ሥራ አስኪያጅ አቶ ፍጹም ከተማ ለኢዜአ ገልጸዋል።

ፕሬዚዳንት ኬንያታ አገሮቹ ግንኙነታቸውን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግና የኢኮኖሚ ትስስራቸውን ለማጠናከር ተቀናጅተው መሥራት እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።

ዶክተር  ዓቢይ  ዛሬ ጠዋት በተካሄደ የኢንቨስትመነት መድረክ ሞያሌን የምስራቅ አፍሪካ የኢኮኖሚ ማዕከል ለማድረግ ከኬንያ ጋር በጋራ  እንደሚሰራ ገልጸዋል።

አገሮቹ ለረጅም ዘመናት የቆየ ግንኙነታቸውን ወደ ላቀ የኢኮኖሚ ትስስር ለማሳደግ እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል።

ፕሬዚዳንት ኬንያታ በኢትዮጵያ ይፋዊ ጉብኝት ለማድረግ አዲስ አበባ የገቡት ዛሬ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም