በወላይታ ሶዶ አንድ ግለሰብ 38 ህገ-ወጥ ቤቶችን ገንብቷል…ከተማ አስተዳደሩ

85

ሶዶ የካቲት 22/2011 በወላይታ ሶዶ ከተማ ህገ-ወጥ ቤቶችን ስርዓት ለማስያዝ የተጀመረው ህግን የማስከበር ስራ እንደሚደግፉ የከተማዋ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡

የከተማዋ አስተዳደር በአካባቢው ወቅታዊ ጉዳይ ዙሪያ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በተወያየበት ወቅት እንደተገለጸው አንድ ግለሰብ 38 ቤቶች በህገ-ወጥ መንገድ ገንብቷል፡፡ 

በውይይቱ ወቅት የከተማዋ ሃገር ሽማግሌ አቶ ገብረ-መድህን ቴቃ እንዳሉት በከተማዋ በሰውና ንብረት ላይ ያደረሱ እንዲሁም ተመሳሳይ ህገ ወጥ ድርጊት ለመፈጸም  የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦችን ማጋለጥ ይገባል።

ለሰላምና ደህንነት ጉዳይ ቅድሚያ በመስጠት በሚኖሩበት አካባቢ ህገወጥ ድርጊት እንዳይፈጸም ህብረተሰቡን በማስተማር ከአጉል ተግባራት እንዲቆጠብ ኃላፊነታቸዉን እንደሚወጡም ገልጸዋል፡፡

በከተማዋ ህግን ለማስከበር በተለይም በህገ-ወጥ የመሬት ወረራ የተገነቡ ቤቶችን ስርዓት ለማስያዝ የተጀመረው ስራ እንደሚደግፉና ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም አመልክተዋል፡፡

የህግ የበላይነትን ለማስከበር መንግስት እየወሰደ ያለው እርምጃ ተገቢ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በከተማዋ የመርካቶ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ጎሳዬ ዛዛ ናቸው፡፡

ከዚህ በፊት ውይይቶች ቢደረጉም ውጤታማ ባለመሆናቸው  ባለቤት የሌለበት ከተማ አድርጎ ይወሰድ እንደነበረም አስታውሰዋል፡፡

አንዳንድ ግለሰቦች ባላቸው ገንዘብ በመመካት ከስግብግብ ደላሎች ጋር እየተመሳጠሩ ህብረተሰቡን በማታለል በመሬት ላይ እንዳሻቸው የሚወስኑበት ሁኔታ ለማስቆም መሰራት እንዳለበት ጠቁመዋል።

በዚህ ሂደትም ህጋዊ ፈቃድ ያላቸዉ ነዋሪዎችም ጉዳት ላይ እንዳይወድቁ የከተማ አስተዳደሩ ታች ድረስ ወርዶ በአግባቡ ማጣራት እንዳለበት አሳስበዋል።

"ካለፈው ዓመት መጨረሻ ጀምሮ የጸጥታ ችግር በመፍጠር ከተማዋን ለማሸበር  ሀሰተኛ መረጃዎችን በማህበራዊ ድረ ገጾች በመልቀቅ የከተማዋን ገጽታ የሚያጠፉ ግለሰቦች ተገቢ ማጣራት ተደርጎ ርምጃ ሊወሰድ ይገባል" ብለዋል፡፡

ሌላው  የውይይቱ ተሳታፊ ወጣት ሃብታሙ ሙኮ  በህጋዊ መንገድ በ2004 ዓ.ም.  የገነባውን መኖሪያ ቤት እሱ በሌለበት እንደፈረሰበት ተናግሯል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተስፋፋ የመጣው የህገ-ወጥ ቤት ግንባታ ከተማውን  ወደ አልተፈለገ  አቅጣጫ እየመራ በመሆኑ ጥንቃቄ እንዲደረግም ጠቁሟል።

የከተማዋ አስተዳደር ምክትል ካንቲባ አቶ ሃንጃላ ደሴ  በአቋራጭ ለመበልጸግ ህገ-ወጥ ግንባታ ላይ በመሰማራት  የህዝብንና የሃገርን ሃብት የሚመዘብሩ ግለሰቦች መበራከታቸውን ተናግረዋል፡፡

ይህም ህግን የማስከበር ስራ ላይ ፈተና እንደሆነባቸው አመልክተዋል።

በተደረገው ማጣራት አንድ ግለሰብ እስከ 38 ቤቶች በህገ-ወጥ መንገድ መገንባቱ እንደተረጋገጠ የገለጹት ምክትል ከንቲባው ችግሩ አብዘኛውን የከተማ ነዋሪ ጥቅም ከማሳጣት ባለፈ ለከፋ ችግር ሊዳርግ እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡

በተደጋጋሚ ከህዝቡ ጋር በተደረገ ውይይት ህገወጥ ግንባታ ያከናወኑ ግለሰቦች በአስቸኳይ እንዲያነሱ ቢነገራቸውም ተግባራዊ ባለማደረጋቸው  እርምጃ እንደተወሰደ ገልጸዋል።

ይህን ተከትሎም ጥቅማቸው የተነካባቸው ህገ-ወጦች በተለያየ ዘዴ ከተማውን ለማወክ እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን ጠቅሰው የከተማው ነዋሪ እያደረገ ያለው ሰላምን የመጠበቅ ተግባር አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

እስካሁን በህገወጥ መንገድ የተገነቡ 757 ቤቶች እንዲፈርሱ መደረጉንና በዚህ ሂደት በስህተት ህጋዊ ይዞታቸው የፈረሰባቸው ካሉ በማጣራት የከተማ አስተዳደሩ ለመካስ ዝግጁ መሆኑን አስታውቀዋል።

በኢንቨስትመንት ስም ቦታ ወስደው ወደ ስራ ሳይገቡ አጥረው ያስቀመጡ ካሉ በማጣራት ተገቢው እርምጃ እንደሚወሰድም  ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም