በደቡብ ኦሞ ዞን የሰሜን አሪ ወረዳ ነዋሪዎች ከሰሩት የተፈጥሮ ኃብት ጥበቃ ተጠቃሚ መሆናቸውን ገለጹ

115

አዲስ አበባ  የካቲት 22/2011በደቡብ ኦሞ ዞን የሰሜን አሪ ወረዳ ነዋሪዎች በተሰሩት የተፈጥሮ ኃብት ጥበቃ ስራዎች ተጠቃሚ መሆናቸውን ገለፁ።

በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል በደቡብ ኦሞ ዞን ሰሜን አሪ ወረዳ የሳላ ቅርጫ ቀበሌ ነዋሪዎች እንደተናገሩት ባለፉት ዓመታት በተሰሩ የተፈጥሮ  ኃብት ጥበቃና የተፋስስ ልማት ስራዎች ምርታማነታቸውን እያሳደገው ነው።

በክልሉ በርካታ አካባቢዎች በነበረው የተፈጥሮ ኃብት መመናመን ሳቢያ ከፍተኛ የምርት እጥረት ይስተዋል ነበር።

ይህንን ሁኔታ ለመለወጥ ላለፉት ስድስት ዓመታት በክልሉ አርሶ አደሮች አማካኝነት በተካሄደው የተፈጥሮ ኃብት ጥበቃና የተፋሰስ ልማት መርሃ ግብር ከ3 ነጥብ 9 ሚሊዮን ሄክታር በላይ የተመናመነ መሬት እንዲለማ ተደርጓል። 

ኮንሶ፣ ጋሞ፣ ጎፋ፣ ሲዳማ፣ ወላይታ፣ ጌዲዮ እና ሌሎች ዞኖች በክልሉ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በተካሄደ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት መርሃ ግብር ውጤት ካስመዘገቡ አካባቢዎች መካከል ናቸው።  

በደቡብ ኦሞ ዞን ሰሜን አሪ ወረዳ የሳላ ቅርጫ ቀበሌ ነዋሪዎችም ከእነዚሀ ተጠቃሚዎች መካከል ይጠቀሳሉ።

በመርሃ ግብሩ አማካኝነት በአካባቢው የተከናወነው የእርከን ስራ የአካባቢው አፈር እንዳይሸረሸር በማድርግ የአካባቢውን ለምነት አጎልበቶታል፤ በዚህም ወጣቶች በመደራጀት የተለያዩ የግብርና ምርቶችን በማምረት ገቢ እያገኙ መሆኑን ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።

ወጣቶቹ ድንች፣ ተልባ፣ አፕል፣ ሽንኩርት፣ የግጦሽ ሳር እና ሌሎች ምርቶችን በማምረት እየተጠቀሙ ይገኛሉ።

ከወጣቶቹ መካከል ብርሃኑ ሀላቢ እንደሚናገረው በዚህ ዓመት ብቻ ማህበራቸው እስከ 70 ኩንታል ድንች ምርት አግኝቷል።

ሌላዋ ወጣት ስንታየው  ኤልቦስ በበኩሏ በወረዳው ህብረተሰብ የተከናወነውን የተፈጥሮ ኃብት ጥበቃ ልማት ተከትሎ የአካባቢው የተፈጥሮ ኃብት ተሻሽሏል። በዚህም ሳቢያ ከሌሎች ዘጠኝ ሴቶች ጋር በመሆን የጀመረችው የድንችና አፕል እንደዚሁም የከብቶች መኖ ሳር ምርት አመረቂ ውጤት እያስገኘላቸው መሆኑን ትናገራለች።

በደቡብ ኦሞ ዞን የሰሜን አሪ የግብርና ጽህፈት ቤት የተፋሰስ ልማት ቡድን መሪ አቶ ሲሳይ ስጦታው በበኩላቸው እንዳሉት በወረዳው ካሉት ተፋሰሶች ውሰጥ በሳላ ቅርጫ ተፋሰስ ልማት በለማው መሬት ላይ ወጣቶች በመስራት ውጤታማ ሆነዋል።

ከዚህ በፊት ግን አካባቢው ለከብት ግጦሽ የሚሆን ሳር እንኳ የማይበቅልበት እንደነበር በማንሳት።

ከዚህም በተጨማሪ በወረዳው የአፈር ለምነትን ለማሻሻል በ14 አሲዳማ ቀበሌዎች ላይ የአፈር ማከም ሰራ በመስራት ምርትና ምርታማነት እየተሻሻለ ነው ብለዋል።

በወረዳው 33 ንዑስ ተፋሰሶች ያሉ ሲሆን በየዓመቱ ከ28 ሺህ ህዝብ በላይ በስነ አካላዊና አካባቢ ጥበቃ ስራ ይሰማራል፤ ሥራውን ለአንድ ወር የሚቆይ እንደሚቆይ ጠቅሰዋል።

በዚህ ዓመትም ስራው ተጠናክሮ ቀጥሏል ነው ያሉት አቶ ሲሳይ።

የሰሜን አሪ ወረዳ ተዳፋት የሚበዛበት በመሆኑ ለአፈር መሸርሸር የተጋለጠ ወረዳ ሲሆን ህብረተቡም ህይን ችግር በመረዳት በፍቃደኝነት በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ እየተሰማራ ይገኛሉ ብለዋል።

በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል የግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ መለስ መና በበኩላቸው እንዳሉት በክልሉ የተቀናጀ ተፋሰስ ልማት መስራት ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ እስከ አሁን ከ3 ነጥብ 9 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በላይ በተፈጥሮ ኃብት ጥበቃና በተፋሰስ ልማት ስራዎች ለምቷል።

ላለፉት ዓመታት የተከናወነው ይህ ተግባር የአካባቢውን ምጣኔ ኃብታዊ አንቀስቃሴ ከማነቃቃት ባሻገር የህዝቡንም ህይወት አየለወጠው ነው ሲሉም ተናግረዋል። በተለይም ሥራ አጥነትን ለመከላከል ዓይነተኛ መሳሪያ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል ነው ያሉት።

በክልሉ በዚህ ዓመትም ከ405 ሺህ 800 ሄክታር በላይ መሬት ለማልማት እየተሰራ ሲሆን ከ4 ነጥብ 8 ሚሊዮን ህዘብ  ይሳታፍበታል ተብሏል።

በመሬቱ ላይም ከ1 ነጥብ 6 ቢሊዮን በላይ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸውን የተለያዩ ችግኞች ለመትከል ዝግጅት ተደርጓል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም