በትራፊክ አደጋ የ18 ሰዎች ህይወት አለፈ - ኢዜአ አማርኛ
በትራፊክ አደጋ የ18 ሰዎች ህይወት አለፈ
108
ደብረብርሃን ግንቦት 22/2010 በሰሜን ሸዋ ዞን አንጎለላ ጠራ ወረዳ ትናንት በደረሰ የትራፊክ አደጋ የ18 ሰዎች ሕይወት ማለፉን የዞኑ ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ። የመምሪያው የ24 ሰዓት መረጃና ትንተና ባለሙያ ኢንስፔክተር አጥናፌ ሐይለስላሴ ለኢዜአ እንደገለጡት አደጋው የደረሰው ትናንት ከምሽቱ 10 ሰዓት ከ40 አካባቢ በወረዳው ሰሪቲ ቀበሌ ውስጥ ነው፡፡ አደጋው ታታ የተሰኘ ሀገር አቋራጭ የሕዝብ ማመላለሻ ተሸከርካሪ ከተቃራኒ አቅጣጫ ከሚመጣ ሃይሩፍ አነስተኛ የህዝብ ማመላለሻ ተሸከርካሪ ጋር በመገጋጨቱ መከሰቱንም ነው ባለሙያው የተናገሩት፡፡ በአደጋው አሽከርካሪውን ጨምሮ በአነስተኛው ተሸከርካሪ ውስጥ የነበሩ 18 ሰዎች በሙሉ ሕይወታቸው አልፏል፡፡ በሀገር አቋራጭ የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪው ውስጥ በነበሩ ተሳፋሪዎች ላይ ምንም ጉዳት እንዳልደረሰባቸው የገለፁት ኢንስፔክተሩ የሟቾች አስከሬን ወደ ዳግማዊ ምኒሊክ ሆስፒታል መላኩን ተናግረዋል፡፡ የአደጋውን መንስኤ ፖሊስ እያጣራ መሆኑንም ጨምረው ገልፀዋል፡፡