ዳግማዊ ምኒሊክ ሪፈራል ሆስፒታል አቋርጦት የነበረውን የኩላሊት እጥበት ዳግም ጀመረ

383

አዲስ አበባ  የካቲት 21/2011 የዳግማዊ ምኒሊክ ሪፈራል  ሆስፒታል በህክምና ግብዓት እጥረት ላለፉት ስምንት ወራት አቋርጦት የነበረውን የኩላሊት እጥበት ዳግም መጀመሩ ተነገረ።

የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ምክትል ሃላፊ ዶክተር ሳሙኤል ዘመንፈስ ቅዱስ ለኢዜአ እንደገለጹት ሆስፒታሉ በህክምና ግብዓት እጥረት ላለፉት ስምንት ተከታታይ ወራት የኩላሊት እጥበት ስራውን አቋርጦ ቆይቷል።

አገልግሎቱን አቋርጦ የቆየው ለኩላሊት እጥበት የሚያገለግሉ የህክምና ግብዓቶች ውድ በመሆናቸው እንዲሁም አገር ውስጥ በቀላሉ የማይገኙ በመሆናቸው ነው ያሉት።

አገልግሎቱ ተቋርጦ በመቆየቱ ታካሚዎች ለእንግልትና ተጨማሪ ወጭ እየተዳረጉ እንደነበር ያስታወሱት ሃላፊው አሁን ግን ሆስፒታሉ ከአጋር ድርጅቶች ጋር በጋራ ለመስራት በገባው ውል የግብአት እጥረቱ በመቃለሉ አገልግሎቱን ዳግም ጀምሯል ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት በሆስፒታሉ የኩላሊት እጥበት ፈላጊዎች ቁጥር 500 ቢደርስም አገልግሎት መስጠት የተቻለው ግን ለ20ዎቹ ብቻ መሆኑንም ጠቁመዋል።

20 ዎቹ ታካሚዎች በድምሩ በሳምንት 60 ጊዜ  የኩላሊት እጥበት አገልግሎት የሚያገኙ ሲሆን መንግስት ከ50 በመቶ በላይ ድጋፍ ያደርጋልም ነው ያሉት።

በከተማዋ የኩላሊት እጥበት አገልግሎት የሚሰጡ የመንግስት ተቋማት ቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ሆስፒታል፣ ጥቁር አምበሳ፣ ዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታልና ዳግማዊ ምኒሊክ ሪፈራል ሆስፒታል ናቸው።

በእነዚህ ሆስፒታሎች አገልግሎቱን ፈልገው የሚመጡ ታካሚዎች ቁጥር በርካታ ቢሆንም አገልግሎት መስጠት የተቻለው ለጥቂቶቹ ብቻ መሆኑን ዶክተር ሳሙኤል ተናግረዋል።

የዳግማዊ ምኒሊክ ሆስፒታል የኩላሊት እጥበት አገልግሎቱን በድጋሚ መጀመሩ ችግሩን በጥቂቱም ቢሆን ለማቃለል አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ይታመናል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም