የአካባቢያቸው ሰላም በማስጠበቅ ሃገራዊ ለውጡን እንደሚያስቀጥሉ የሰቆጣ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ

63

ሰቆጣ የካቲት 21/2011 የተጀመረው ሀገራዊ የለውጥ ጎዞ ሳይደናቀፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የአካባቢያቸውን ሰላም በማስጠበቅ የድርሻቸውን እንደሚወጡ የሰቆጣ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡

የሰቆጣ ከተማ አስተዳደር የከተማውን ሰላምና ጸጥታ አስመልክቶ ትናንት ከከተማው ነዋሪዎች ጋር ተወያይቷል።

በእዚህ ወቅት ነዋሪዎቹ እንዳሉት በተለያዩ ምክንያቶች የሚነሱ የጸጥታ ችግሮች የህዝብ ተጠቃሚነትን ስለሚያደናቅፉ ለሰላም ትኩረት ሰጥቶ ለመስራት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

በከተማው የቀበሌ 01 ነዋሪ አቶ ተፈሪ ገብረእግዚአብሔር እንዳሉት የአካባቢያቸውን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ ከጸጥታ አካላት ጋር እየሰሩ ነው፡፡

" በሃገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች በሚስተዋለው የጸጥታ መደፍረስ ምክንያት ዜጎች ከቤት ንብረታቸው እንዲፈናቀሉ አድርጓል፤ በዚህም ሴቶች እና ህጻናት የችግሩ ግንባር ቀደም ገፈት ቀማሽ ሆነዋል፤ ችግሩ በእኛ ላይ እንዲደርስም አንፈልግም" ብለዋል፡፡

በዚህም በአካባቢያቸው ለጸጥታ ችግር ምክንያት የሆኑ ጉዳዮችን ለመከላከል ከሚመለከታቸው የህግ አካላት ጋር በመሆን የሽምግልና ሥራ እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ሕብረተሰቡ ለዘመናት ያካበተውን በጎ እሴቶችን በማጠናከርና ችግሮችን በውይይት በመፍታት የከተማዋን ሰላምና ሀገራዊ ለወጡን ለማጠናከረ እንደሚሰሩም አመልክተዋል፡፡

ወጣት ሃብቱ በሬ በበኩሉ "ለአካባቢያችን ሰላም መረጋገጥ በተለይ ወጣቱ ይበልጥ ኃላፊነት ወስዶ ሊሰራ ይገባል" ሲል ተናግሯል፡፡

በሀገሪቱ እየተካሄደ ያለው የለውጥ ጉዞ እስከ ታችኛው የህብረተሰብ ክፍል ድረስ ወርዶ ተግባራዊ እንዲሆን የሰላምና ጸጥታ ጉዳይ አማራጭ የሌለው በመሆኑ ይህንንም ለማረጋገጥ የድርሻውን እንደሚወጣ ገልጿል፡፡

በተለይ በአካባቢው ሰላምን በዘላቂነት ለማረጋገጥ በሚከናወኑ ተግባራት የበኩሉን ሚና በመጫወት ኃላፊነቱን እንደሚወጣ ነው የተናገረው።

እንደወጣቱ ገለጻ በከተማዋ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት እጥረትና በሥራ ፈጠራ ዙሪያ ለሚነሱ ጥያቄዎች መንግስት መፍትሄ በመስጠት ለሰላም መደፍረስ ምክንያት የሆኑትን ስጋቶች መቀነስ ይኖርበታል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ አቶ በኃይሉ መኮንን በበኩላቸው በሃገሪቱ የመጣውን ለውጥ ለማስቀጠል በህብረተሰቡ የሚነሱ የልማትና መልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

"የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሰላምና የፀጥታ ጉዳይ ዋነኛው በመሆናቸው ለፀጥታ መደፍረስ ምክንያት ይሆናሉ የተባሉ ጉዳዮች ተለይተዋል" ብለዋል፡፡

በተለይም የሥራ ፈጠራ፣ የመሰረተ ልማት አቅርቦትና የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን በሦስት ወራት ጊዜ ውስጥ ለመፍታት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑንም ነው ያመለከቱት፡፡

"የመጣውን ሀገራዊ ለውጥ ዳር ለማድረስ በየደረጃው ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ለሰላም ዘብ ሊቆሙ ይገባል" ያሉት ምክትል ከንቲባው ለሰላም ስጋት የሆኑ ጉዳዮችን ቀድሞ ለመከላከል ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ወጣቱ ትውልድ ከቀደምት አባቶቹ የወረሰውን የመከባበር እና የመቻቻል እሴት በማጠናከር ለሀገሪቱ ሰላም ዘብ ሊቆሙ እንደሚገባ የገለጹት ደግሞ የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዋና አስተዳዳሪ አቶ በሪሁን ኪዳነማሪያም ናቸው፡፡

አቶ በሪሁን እንዳሉት የህብረተሰቡን የመሰረተ ልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከክልልና ከፌደራል አካላት ጋር በትኩረት እየተሰራ ነው፡፡

በመንግስት መስሪያ ቤቶች ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ ህብረተሰቡን ለእንግልትና ላልተገባ ወጪ የሚዳርጉ አካላት ላይም እርምጃ እንደሚወሰድ አመልክተዋል።

የአካባቢውን ሰላምና ፀጥታ ለማስጠበቅ አስተዳደሩ የብሔረሰብ አስተዳደሩን ከሚዋሰኑ ዞኖች ጋር ተቀራርቦ እየሰራ መሆኑንም ዋና አስተዳዳሪው ጠቁመዋል፡፡

በውይይት መድረኩ ላይ በከተማዋ የሚኖሩ የሃገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማት አባቶች፣ ነጋዴዎች፣ ወጣቶች እና ተማሪዎች ተሳታፊ መሆናቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም