ዩኒቨርሲቲው በእንግዳ አቀባበልና ሆቴል አስተዳደር ትምህርት ተማሪዎችን ተቀብሎ በመጀመሪያ ዲግሪ ማስተማር ሊጀምር ነው

52
ሶዶ ግንቦት 21/2010 ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ በእንግዳ አቀባበልና ሆቴል አስተዳደር ትምህርት ተማሪዎችን በመጀመሪያ ዲግሪ ተቀብሎ ለማስተማር ቅድመ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን አስታወቀ። ዩኒቨርሲቲው ትምህርቱን ለመጀመር ባዘጋጀው ሥርአተ ትምህርትና ባከናወናቸው የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ላይ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ከተጋበዙ ምሁራንና ከባለድርሻ አካላት ጋር ዛሬ መክሯል። የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ተወካይ ዶክተር ወንድሙ ወልዴ "የአካባቢውን ማህበረሰብ ጥያቄ መነሻ በማድረግና በዘርፉ ያለውን ዕምቅ ሃብት በዕውቀት ለማስተዳደር ትምህርት ክፍሉን መጀመር አስፈላጊ ሆኗል" ብለዋል፡፡ ይህም ማህበረሰቡ ከዘርፉ የሚያገኘውን ተጠቃሚነት ከፍ ለማድረግ የሚያስችል መሆኑን ነው የገለጹት፡፡ ከከተማ አስተዳደሩ በተሰጠ 20 ሄክታር መሬት ላይ የሚያርፍ ለማስተማሪያ የሚሆን ሆቴል በማራ ጫሬ ቀበሌ ለማስገንባት የዲዛይን ስራዎችን ማጠናቀቁንም አስታውቀዋል። እንደ ዶክተር ወንድሙ ገለጻ የማስተማሪያ ሆቴሉ ግንባታ በቀጣይ ሦስት ዓመታት እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል፡፡ ሥርአተ ትምህርቱ የአገር አቀፍ ስርዓተ ትምህርትና ፖሊሲን ግምት ውስጥ ከማስገባት ባለፈ አገራዊ ምላሽ እንዲሰጥ ተደርጎ መቀረጹን የተናገሩት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ዲን አቶ ታርኩ ቆልቻ ናቸው፡፡ ዩኒቨርሲቲው የሆቴሉ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ድረስ በ2011 የትምህርት ዘመን ከ30 በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ በራሱ ግቢ ውስጥ ማስተማር እንደሚጀምር አስታውቀዋል፡፡ ተማሪዎችን በንድፈ ሃሳብና በተግባር ለማስተማር በአሁኑ ወቅት የመምህራን ቅጥርና አስፈላጊ ግብአቶች እየተሟሉ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ በመድረኩ ከተሳታፉ ምሁራን መካከል ከሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ እንግዳ አቀባበልና የሆቴል አስተዳደር ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር አማረ ነጋ አንዱ ናቸው፡፡ "እንደአገር በተለይም የደቡብ ክልል ዓለምን መሳብ የሚችልና ዕምቅ የሆነ የባህል ሃብት እያለው በተሻለ መጠቀም ያልተቻለው ዘርፉ በሳይንሳዊ መንገድ አለመመራቱ ነው" ብለዋል፡፡ በክህሎት የሚመራና የተማረ የሰው ኃይል አለመፈጠር፣ በመንግስትም ሆነ በግል ደረጃ በዘርፉ የተሰማሩ ግለሰቦች የቅንጅትና የትኩረት ማነስ እንዲሁም የአገር ውስጥ ቱሪስት መዘንጋቱ የዘርፉ ፈተናዎች መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በዘርፉ ተማሪዎችን ተቀብሎ ማስተማር ሲጀምር ለችግሮቹ በተወሰነ መልኩ መፍትሄ ይሰጣል የሚል እመነት እንዳላቸውም ጠቁመዋል። ወላይታ ሶዶ ከተማ ለደቡቡ አብዛኛው አካባቢዎች መተላለፊያ ማዕከል መሆን የሚችል በመሆኑ በዙሪያው ላይ የሚገኙ ብሔረሰቦችን ዕሴት ማሳየት የሚችል ሙዚየም ዩኒቨርሲቲው ማደራጀት እንዳለበትም አመልክተዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም