ልዩነትን በማጥበብ ለሃገር መስራትን ከአድዋ ጀግኖች እንማር ---የአክሱም ዩኒቨርሲቲ ምሁራን

64

መቀሌ የካቲት21/2011 ኢትዮጵያዊያን ከአድዋ ጀግኖች በመማር ልዩነታችንን አጥብበን በአንድነት ለሃገራችን እድገት ብዙ መስራት ይጠበቅብናል ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የአክሱም ዩኒቨርስቲ ምሁራን ገለጹ።

የአድዋ ድል ታሪክ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲሸጋገር ሁሉም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣም ምሁራኑ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

የአክሱም ዩኒቨርስቲ የታሪክ ተመራማሪና መምህር ዮርዳኖስ ሙሉጌታ እንዳሉት፣ ታላቁ የጥቁር ህዝቦች የዓድዋ ድል በመላው አለም ፖለቲካ በነበረው የቅኝ አገዛዝ ስርአት ላይ ከፍተኛ ለውጥ ያመጣ ነው።

“ድሉ ከታሪካዊነቱ አንጻር ተገቢውን ትኩረት እንዳልተሰጠው ያመለከቱት ምሁሩ፣በአመት አንዴ ከማክበር ባሻገር ትክክለኛው ታሪክ ተጽፎ፣ተሰንዶና ሙዚየም ተሰርቶለት ለቱሪስት መስህብነት ጥቅም ላይ እንዲውል መደረግ አለበት” ብለዋል።

“የዓድዋ ድል ትልቅ የዓለም ቅርስ ነው” ያሉት መምህር ዮርዳኖስ፣ድሉን የሚዘከር ዘመናዊ ሙዚየምና የተደራጀ ቤተ-መጽሐፍት ሊገነባ እንደሚገባም ጠቁመው እሳቸውን ጨምሮ ምሁራን ታሪኩን ጽፈው ለትውልድ ለማስተላለፍ መስራት እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል።

“የአድዋ ድል ለመላው አፍሪካዊያንና ለሌሎች የአለም ጥቁር ህዝቦች ድልና የነጻነት መሰረት በመሆኑ ኢትዮጰያዊያን ልዩነታችንን በማጥበብና አንድነታችንን በማጠናከር ለሃገራችን እድገት መስራት ይጠበቅብናል” ብለዋል።

በዩኒቨርሲቲው የታሪክና ቅርስ አስተዳደር መምህር ግርማይ ሓለፎም በበኩላቸው ”በአድዋ ጦርነት ላይ በሰሩት ትልቅ ጀግንነትና መልካም ስራ ልክ ታሪካቸው ያልተነገረላቸውና ያልተጻፈላቸውን ጀግኖችን ሁሉም ማስታወስ ይገባል” ብለዋል።

በአድዋ ጦርነት ወቅት መላው የኢትዮጵያ ህዝቦች እንደተሳተፉ ያስታወሱት መምህር ግርማይ፣ለማሸነፍ ለድሉ መገኘት ከፍተኛ አስተዋጽኦ የነበራቸው አርበኞችን ህዝብ እንደማይረሳቸው ተናግረዋል።

መምህሩ አያይዘውም የእነ ባሻይ አውዓሎም የስለላ ስራ፣የእነ ጀነራል አሉላ አባነጋ፣ደጃዝማች ባልቻ አባነፍሶ፣የእነ ራስ መንገሻ ዮሃንስ ፣ፊት አውራሪ ገበየሁ እና ንጉስ ተክለሃይማኖት የታሪክ ስራዎች አስተዋጽኦ እስካሁን በአግባቡ እንዳልተጻፈ ተናግረዋል።

ከአድዋ ጦርነት በፊት በጉራዕ፣በዶግዓሊ፣በጉንደት በጉፊትና በመተማ ዮሃንስ የተደረጉ የነጻነት ተጋደሎዎችም ተኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ ነው ምሁሩ ያስታወሱት።

በቀጣይም የታሪክ ምሁራን ኢትዮጵያውያንን የሚያቀራርቡ ታሪኮችን በመጻፍና በመሰነድ ለትውልድ ሊያስተላልፉ እንደሚገባ ገልጸው ጥናትና ምርምር በማካሄድ የአድዋ ድል ታሪክን ለቱሪዝም ልማት ለማዋል የድርሻቸውን እንደሚወጡ አስረድተዋል።

“የታሪክ ምሁራን ታሪክን ለፖለቲካ ፈጆታና ለአንድ ወገን ሲያዳሉ ይታያል” ያሉት መምህር ግርማይ፣የኢትዮጵያ ታሪክ በትክክለኛነት ተጽፎ ሙያዊ ትንታኔ በማስቀመጥ ለቀጣይ ትውልድ ማስተማር እንደሚገባ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም