ድጋፍ በማጣት መቸገራቸውን ተፈናቃዮች ገለጹ

67

ደሴ/ደብረማርቆስ የካቲት 21/2011ተገቢውን ድጋፍ በማጣት ለችግር መጋለጣቸውን ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ተፈናቅለው በደቡብ ወሎና ምስራቅ ጎጃም ዞኖች የሚገኙ ሰዎች ገለጹ፡፡

በደቡብ ወሎ ዞን በጊዜያዊ ማቆያዎች ከሚገኙት መካከል አቶ መሃመድ ሰይድ ለኢዜአ እንዳሉት ጂግጂጋ አካባቢ ተፈጥሮ በነበረው ችግር ተፈናቅለው  በሐይቅ ከተማ ባለው መጠለያ  መኖር ከጀመሩ አምስት ወራት ሆኗቸዋል፡፡

ከሁለት ወር በፊት በቤተሰብ ቁጥር ልክ ለአንድ ሰው 15 ኪሎ ግራም ስንዴ በመንግስት ድጋፍ ከተደረገላቸዉ ውጪ  ድጋፍ እንዳላገኙ ተናግረዋል፡፡

ወጣቱ የአካባቢውን ህብረተሰብ በማስተባበር በሚያደርግላቸው የዕለት ደራሽ ድጋፍ ህይወታቸውን  ማቆየት ቢችሉም  አሁን ድጋፉ በመቋረጡ ለችግር መጋለጣቸውን ገልጸዋል፡፡

ያሉበት መጠለያ የተጨናነቀ በመሆኑ የጤና መታወክ እንዳጋጠማቸው አመልክተው መንግስት የችግራቸውን አሳሳቢነት ተረድቶ በዘላቂነት አንዲቋቋሙ  አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጣቸዉም ጠይቀዋል፡፡

ሌላው በኮምቦልቻ ከተማ ወጣቶች ማዕከል ጊዜያዊ መጠለያ የሚገኙት  አቶ አባተ ሙላት በበኩላቸው 248 ተፈናቃዮች አንድ ላይ እንደሚኖሩ ጠቅሰው ከሁለት ወር በፊት መንግስት የሰጣቸው የምግብ ድጋፍ በማለቁ መቸገራቸውን ተናግረዋል፡፡

" የእለት ጉርሳችን ያደርሰን የነበረው የአካባቢዉ ህብረተሰብ ሰልችቶት ድጋፉን በማቋረጡ ስድስት የቤተሰብ አባላትን  ይዤ ለችግር ተጋልጫለሁ” ብለዋል፡፡

መንግስት ዘለቄታዊ መፍትሄ እንዲሰጣቸውም ጠይቀዋል፡፡

የዞኑ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ተጠሪ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ወርቁ ይማም በበኩላቸው ከሁለት ወራት በፊት 511 ብቻ የነበሩት የተፈናቃዮች አሁን ላይ ሁለት ሺህ 100 መድረሳቸውን ገልጸዋል፡፡

አቶ ወርቁ እንዳመለከቱት ሁሉንም ተፈናቃዮች በመጠለያ ለማሰተናገድ ቢከብድም ለመደገፍ ከሁለት ወር በፊት ከክልል የተላከውን 289 ኩንታል ስንዴ በሰው 15 ኪሎ ግራም ለማዳረስም ተሞክሯል፡፡

የወሎ ዩኒቨርስቲም  280 ኩንታል መኮረኒ፣ ሩዝና ፓስታ እንዲሁም ዘይት ድጋፍ ማድረጉን ጠቅሰው የጤና ችግር የገጠማቸውም ከዞኑ ጤና መምሪያ ጋር በመተባበር   ነጻ የህክምና እርዳታ እንዲያገኙ እየተሰራ  ነው፡፡

ህብረተሰቡ ጭምር  ድጋፍ እያደረገ ቢሆንም ከብዛታቸው አንጻር በቂ ባለመሆኑ የከልሉ መንግስት ተጨማሪ እርዳታ እንዲያቀርብ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡

ተፈናቃዮች ወደ ቀደመ ቦታቸው ለመመለስ ከመጡባቸው ክልሎች  ጋር ለመወያየትና መልሶ ለማቋቋም እየተሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

በተመሳሳይ ችግር በምስራቅ ጎጃም ዞን  የሚገኙ ተፈናቃዮች  ተገቢው ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል።

ተፈናቃዮቹ ከሶማሌና ቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልሎች እንደመጡ  ገልጸው የሚደረግላቸው የምግብ እህል ድጋፍ በቂ ባለመሆኑ ከነቤተሰባቸው ተቸግረው እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡

የእለት ደራሽ እርዳታ እንዲሟላላቸውና በዘላቂነት ሰርተው  ኑሯቸው  በተረጋጋ ሁኔታ ለመምራት መንግስት የስራ እድል እንዲፈጠረላቸውም ጠይቀዋል፡፡

የዞኑ ምግብ ዋስትና እና አደጋ መከላከል ተጠሪ ጽፈት ቤት  ኃላፊ አቶ መግባሩ ውዴ ከተለያዩ የሀገሪቱ አከባቢዎች ተፈናቅለው ወደዞኑ የመጡ ከ1ሺ300 በላይ ሰዎችን በመንግስትም ሆነ በአጋር አካላት ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

እስካሁንም  220 ኩንታል ስንዴ እና በቆሎ እንዲሁም 400 ሊትር የምግብ ዘይት ፥ከ200 በላይ ብርድልብስ   ድጋፍ  ተደርጓል።

ኃላፊው እንዳሉት ወደነበሩበት መመለስ ለማይፈልጉ  ተደራጅተው መስራት እንዲችሉ በፍላጎታቸውን መሰረት  ከ200 በላይ ተፈናቃዮችን ማሰልጠን ተችላል።

የቦታ እና የገንዘብ አቅርቦት እንዲመቻችላቸው በዞን ደረጃ ተወስኖ እንቅስቃሴ መጀመሩን አመልክተው  ከ20 በላይ የመንግስት ሰራተኞችም ባላቸው ሙያ በየወረዳው መስሪያ ቤቶች እንዲቀጠሩ መደረጉን ጠቅሰዋል።

የምግብ እህል  አቅርቦት እጥረት ለማስተካከል ጥረት እየተደረገ ነው፡፡፡

የደብረማርቆስ ከተማ አስተዳደር ጥቃቅን እና አነስተኛ ጽፈት ቤት ኃላፊ አቶ ምንያምር አባይነህ በበኩላቸው ለ30 ተፈናቃዮች 5 ሺህ ካሬ ሜትር የመስሪያና የመሸጫ ቦታ እንዲሁም የገንዘብ ብድር አገልግሎት እያመቻቹ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም